
በምድር ላይ ያለን ክርስቲያናዊ ሚና፦ ምድርን ማልማት ወይስ ወንጌልን መስበክ?
በዶ/ር ተካልኝ ነጋ አንጎሬ
እንደ ክርስቲያን በምኖርባት ምድር ላይ ሚናዬ ምንድን ነው? ይህን ጥያቄ በዘመናችን የአምላካችንን ፈቃድ ፈጽመን ማለፍ የምንፈልግ ሁላችንም እናሰላስላለን። ጥያቄው ኃላፊነትን ለማወቅ የመፈለግ ነውና ተገቢ ነው። ተቆጥሮ በተሰጠ ዕድሜ እንደሚኖር ሰው፣ በእርግጥም ይህን ጥያቄ ማሰላሰልም መመለስም ይገባል። በዚህች ምድር ስኖር የሚጠበቅብኝ ኃላፊነት ወይም ትእዛዝ ምንድን ነው? በሌላ አነጋገር በዘመኔ እንድፈጽመው የተሰጠኝ ኃላፊነት አለ ወይ? የአብዛኞቻችን መልስ “አለ” የሚል ነው፤ “ምንድን ነው?” በሚለው ላይ ግን ልዩነት አለን። በዚህ መጣጥፍም ኃላፊነቶቻችችን የምንድን ናቸው? የሚሉትን ልዩነቶቻችንን እናነሳለን።
የኃላፊነት ጥያቄውን ስንመልስ የምንነሳው ከሰውነታችን ነው። የሰውነታችን ግንዛቤ የሚመዘዘውም ከአባታችንና ከእናታችን ከአዳምና ከሄዋን ነውና ፊታችንን ወደ ዘፍጥረት እናቀናለን። የፍጥረት መጽሐፍ ለሰው የሰጠው ኃላፊነትም “ምድርን ግዙአት” የሚለው ሆኖ ይገኛል (ዘፍጥረት 1፡26-28)። ከዚህም የሰው ልጅ ኃላፊነት ምድርን የማልማት ሆኖ ይገኛል። ተልእኳችንም ምድርን አምላክ በሚፈልገው መልኩ ማበጀት ነው ወደሚለው ድምዳሜ ይወስደናል።
ከውድቀት በኋላ ለተገኘን ሰዎች ተልእኳችንን ለማግኘት ፊታችንን ወደ ፍጥረት መጀመሪያ እናቅና የሚለው ሐሳብ የማይዋጥላቸው ክርስቲያኖች ግን አልጠፉም፤ እንደውም በወንጌላውያን አካባቢ በቁጥርም ብዙ ናቸው። መከራከሪያም አላቸው። እነዚህ “ምድርን ማልማት ለሰው የተሰጠ ዋነኛ ኃላፊነት ነው” ሲባል የማይጥማቸው ብቻ አይደሉም፤ መረዳቱን እንደ “ሐሰተኛ ትምህርት” የፈረጁትም ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ለሰው ልጅ በግልጽ የተሰጠውን ትእዛዝ እንዴት የሐሰት ትምህርት ሊሉት ቻሉ? ሁለቱን ዋነኛ ምክንያቶቻቸውን እንምዘዝ። አንደኛው፣ የዘፍጥረቱ ትእዛዝ ከውድቀት በፊት የነበረና ከውድቀት በኋላ ላለነው ለእኛ እንደ መርህ ሊያገለግል አይችልም የሚል ነው። ስለዚህም ከውድቀት በኋላ ለምንኖር ለእኛ ለሰዎች የሚያገለግል ትእዛዝ አይደለም። “ፍጥረት መጀመሪያ ላይ ከነበረው ዓለምና ሁኔታ ጋር ተለያይተናል” ሲሉ ይሞግታሉ። ከዚያ ዓለም ጋር ዳግም የምንገናኘው ጌታ ዳግም ከተመለሰ በኋላ ብቻ ነው ሲሉም ይሟገታሉ።
ትእዛዙ ከውድቀት በፊት የነበረና ከውድቀት በኋላ ላለነው ለእኛ አያገለግልም የሚለውን ሙግት ለማጠናከርም የሚያቀርቧቸው ዝርዝር መከራከሪያዎች አሏቸው። አንዳንዶቹ “የምድርን ግዛት ሕግ ለኖህ በተሰጠው ትእዛዝ ውስጥ ሳይጠቀስ አልፏል” ይላሉ (ዘፍጥረት 9)። ለእነዚህ፣ ከቀደመው ትእዛዝ እንድንፈጽመው የቀረልን ነገር የመባዛቱና ምድርን የመሙላቱ ብቻ ነው። ሌሎቹ “ምድርን ግዙአት” የሚለው ቃል በኖህ ቃል ኪዳን ውስጥ አለመጠቀሱ፣ የመግዛት ጽንሰ-ሐሳብ ከመብዛትና ምድርን ከመሙላት ያለፈ ነገር ቀድሞውንም እንዳልነበረው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።
ትምህርቱን የሐሰት ትምህርት አድርገው እንዲበይኑት ያደረጋቸው ሁለተኛው ምክንያትም፣ ይህንን ማመን ጌታችን ከሰጠን ከአዲሱ ትእዛዝ እንድናፈነግጥ ወይም ትኩረታችንን እንድናነሳ ያደርገናል ከሚል ሥጋት ይመነጫል። ለእነዚህ አዲሱ የጌታችን ትእዛዝ “ወንጌልን ስበኩ” (ማቴዎስ 28፡19-20) የሚለው ነው። ስለዚህም ማስተማርም ማክበርም ያለብን ጌታችን ያዘዘንን አዲሱን ትእዛዝ ነው ሲሉ ይሟገታሉ። ስለዚህም ከውድቀት ጀምሮ እስከ ዳግም ምጽአት ባሉት ጊዜያት ዋነኛ ኃላፊነታቸው የእግዚአብሔርን ጽድቅ መመስከር፣ የቅድስና ኑሮን መኖርና በሚቻለው መንገድ ሁሉ ሰዎች የአዳኙን እውቀት እንዲያገኙ መርዳት ነው ሲሉም ይሟገታሉ።
ወንጌልን ከመመስከር ተልእኮ ትኩረታችን እንዳያፈነግጥ ማለት አንድ ነገር ነው። ከዚህ ፍርሃት በመነሳት ግን “ለሰው ልጅ የተሰጠው ተልእኮ እኛን አይመለከተንም” ማለት ግን ይዞት የሚመጣው በርካታ አደጋዎች አሉት። አምላክ በስድስቱ ቀናት የጀመራቸውን ነገሮች የማቃናትና የማበጀት ኃላፊነታችንን የሚያስጥለን ነው። እርሱ ብርሃንን ከጨለማ እንደለየና ደረቁን ምድር ከውኃ በመለየት ምድራችንን አመቺ እንዳደረገ ሁሉ፣ እኛም መልኩን እንደሚያንጸባርቅ ፍጥረት ምድርን አመቺና የተሻለች የማድረግ ኃላፊነት አለብን ብለን እንዳናምን ያደርገናል። በፍጥረት ውስጥ የአብሮ ሠራተኝነት ኃላፊነት ተካፍለናል ብለን ስናምን፣ ተራ የሚመስለው የዕለት ተዕለት ጉዳይና ተግባር በፊታችን እጅግ የከበረና መንፈሳዊ ትርጉም ያለው ይሆናል። ይህንን ትእዛዝ እንደ አምላካዊ ትእዛዝ ችላ ስንለው፣ የምንከውነው ብዙ ተግባር በዓይኖቻችን ፊት እጅግ ይቀላል። የምንፈጽመውም መኖር ስላለብንና መኖር ደግሞ መብላትና መጠጣትን ግድ ስለሚል ብቻ ይሆናል።
ከውድቀት በፊት ለሰው የተሰጠው ትእዛዝ የእኛም ነው ብለን ስናምን፣ የትኛውም ኃላፊነት በዓይናችን ፊት የከበረና በብዙ አክብሮት የምንፈጽመው የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ እንገነዘባለን። የዘፍጥረት ትእዛዝ ለእኛም ነው ብለን ስናምን ራሳችንን በምድር ላይ የአምላክ ወኪል አድርገን እናያለን። ራሳችንንም የአምላክ ተባባሪዎች አድርገን እናያለን፤ አስተዳደራችንም መጋቢያዊ ይሆናል። ዘፍጥረት ላይ ያለው ትእዛዝ ለእኛም ከሆነ፣ የዘፍጥረቱ የአታክልት ስፍራ (ገነት) ገና ጅማሬና ፍጥረት ልትሆን የምትችለውን አቅም ጥቆማ ሆኖ ይታየናል። የእኛም የማበልጸግና የማሻሻል ኃላፊነት ከአምላክ ጋር የመተባበር እንደሆነ እንረዳዋለን።
ጌታችንም “ሁለተኛው አዳም” የተባለው ያለምክንያት አይደለም። በእርሱ አምላክ በፍጥረቱ የጀመረው ፍጥረትን የማስተካከል ሥራ መልሶ መቀጠሉን ጠቋሚ ነው። በእርግጥም ለእርሱ ሁሉ ተገዝቶለታል (ዕብራውያን 2፡5-9); ለእኛም ፍለጋውን ትቶልናል። ስለዚህም ወንጌልን መስበክና ምድርን ማልማት እንደ ተቃራኒ ግቦች መቅረብ አይገባቸውም። ሁለቱም ጌታን በማሰብና እርሱን በማክበር ስሜትና መረዳት ሊደረጉም ይገባል። ሥራችንንም የምንናገረውና የምናውጀው ወንጌል ፍሬ የሚያፈራበት መስክ አድርገን ልንረዳው እንችላለን። መልካምን ማድረግ ልክ ወንጌልን እንደመስበክ ሁሉ በእርግጥም ከአምላክ የተቀበልነው ብሎም ልንፈጽመው ዕለት ተዕለት የምንተጋው ኃላፊነት እና ትእዛዝ ነው፤ሥራችንም ከአምላክ የተቀበልነው ትእዛዝም ነው።
Written by : Dr. Tekalign Nega
Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.
Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.



ጠቃሚ እና ምክንያታዊ ጽሑፍ ከመሆኑም ሌላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እዉነት ነዉ፡፡ አንዳንዶች ሙሉ ጊዜና ግማሽ ጊዜ አገልግሎት ወይም መንፈሳዊና ምድራዊ/ሥጋዊ በማለት መስመር ስላበጁ ይህ በወንጌላዊ አማኝ ዘንድ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡ የዚህ አደገኛ አቋም እድገቱ አሁን ላለንበት ስሑት ወንጌል ስብከት ወይም የብልጽግና ወንጌል ላይ መድረሱ ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ እንድከሰት ግዴታ የሆነዉ ለምድራችን ቸልተኞች ሆነን ለሰማያዊዉ ቀናተኞች መስለን መገኘታችን ነዉ፡፡ በተቻለ መጠን ያነሳኸዉ ሀሳብ ይህንንም እንዳይ አርጎኛልና ተባረክ፡፡
It is an important message, we are here on earth to serve God according to our talents. That is to make a difference as well as preach the gospel. God bless you more!