
ደህና አይደለሁም!
በዶ/ር ተካልኝ ነጋ አንጎሬ
የሰሞኑን እኔን እየወደድኩት አይደለም። ቁጣዬም፣ ያውም ጽድቅ ያልሆነው ቁጣዬ፣ ከመቼውም በበለጠ ፍጥነት ሲቀሰቀስ እና ያለ ተገቢ ምክንያት ሲጦዝ አግኝቸዋለሁኝ። ከዚህ ቀደም በቀላሉ ስቄ የማልፋቸውን ነገሮች ማለፍ ሲያቅተኝ ራሴን ተመልክቼዋለሁ፤ ለራሴም ሆነ ለሌሎች ድካም የማሳየውን ርህራሄም አጥቼዋለሁኝ፤ በወጉ ባለየሁትም ምክንያት ሰውነቴ ውጥር ሲል ይሰማኛል።እነዚህ ሁሉ ደግሞ የጤናማነት ምልክቶች አይደሉም። ደህና አለመሆኔንም ያሳያሉ።
የማልወደውን እኔን እየሆንኩ ሳገኘውም ደግሞ ሁሌ እንደማደርገው ራሴን መጋፈጥ ነበረብኝ። “ምን ብሆን ነው ግን እንዲህ የሆንኩት?” “ደግሞስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ብዬም ራሴን ጠይቄያለሁኝ። አሰላስሎዬ እና ውጤቱንም ለአንድ ሰው እንኳን ቢጠቅም በሚል ስሜት ያለ አንዳች ሥሥት አካፍላችኋለሁኝ።
ምን እየሆነ ነው?
ከእንግዳው ሥሥነቴ ጀርባ ያለውን ፈልጌ ያገኘሁት ዐይነተኛው ምክንያት ድካም ሆነ። ለካ አቅሜ ከውስጤ ተንጠፍጥፎ እያለቀ ነበር፤ በቂ እንቅልፍ እየተኛው አልነበርም፤ ስሜቴም እጅግ ተዳክሟል። ስለተዳከምኩ ወይም የድሮው ጥንካሬዪ አብሮኝ ስለሌለም ሁሉም ነገር ከቁጥጥሬ ውጭ የወጣ ዓይነት ስሜትን ፈጥሮብኛል።በጥንካሬዬ ጊዜ በቀላሉ በምረታቸው ነገሮች የመረታቴም ሚስጥርም አቅም ማጣት ነው።
የፈውሴ መጀመሪያም ያለሁበትን እውነታ መቀበል ነው። አዎን ደክሞኛል ማለት ነበረብኝ። የባዘንኩት እና ደከምኩት ግን በአካል ብቻ አልነበረም፤ በስሜትም ጭምር ተዳክሜ ነበር። ሳላስተውለው ለካ ኃይሌ ከውስጤ ተንጠፍጥፎ እያለቀ ነበር። ችግሬም ሳልተካ በቸርነት በመስጠቴ መቀጠሌ ነበር። ሰው ነኝና አለመተካቴ ባዶ አደረገኝ፤ ባዶነት ደግሞ የሚሰጥ ነገር አይደለም፤ ለተቀባዩም ይጎረብጣል።
ነገሩን ለማስረዳትም ደምን መስጠትን ላንሳ። ደም ሰጥታችሁ የምታውቁ የጤና ባለሙያዎቹ ደም ከሰጣችሁ በኋላ እንድትፈጽሟቸው ግድ የሚሏችሁ ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ለሚሆን ጊዜ እረፍት እንድታደርጉ ያዙዋችኋል። ሁለተኛው ከመንቀሳቀሳችሁ በፊትም ፈሳሽ እንድትወስዱ እና ስናክ እንድትቀማምሱ ያደርጓችኋል። እነዚህን ምክሮች ባትከተሉስ? ራሳችሁ ልትስቱ፣ ሊያቅለሸልሻችሁ እና ምድሩና ሰማዩ ሊዞርባችሁ ይችላል። እነዚህ ምልክቶች ከታዩባችሁም ችግሩ ደም መስጠቱ ሳይሆን ራሳችንን ማሳረፍ አለመቻልና ያወጣነውን ኃይል መተካት አለመቻሉ ነው። የኔም ችግር የሀኪሞቹን ምክር ካለመከተል ጋር ይመሳሰላል።
ምን ላድርግ?
ሰሞኑን ሕይወቴ ውስጥ ያየሁት ነገር የዘነጋሁትን ነገር እንዳስታውስ ረድቶኛል። ለሥራዬ እና ለቤተ ሰቤ ሳልሰስት ስሰጥ ለራሴ ግን ንፉግ የምሆንበት ዕድል መኖሩን አመላክቶኛል። ስለሌሎች ሳስብ ለካ ራሴን እየዘነጋሁት ነበር። ትኩረቴ ሁሉ ቀኑ እንካህ የሚለኝን ኃላፊነቶች ላይ ሆነ። ከመጠን በላይም መፈጸም ያሉብኝ ተግባሮች ላይ ብቻ አተኮርኩ፤ በሂደቱም ራሴን መንከባከቡን ዘነጋሁት።
ከዘነጋኋቸው እና ዋጋ እያስከፈሉኝ ካሉ ነገሮች መካከል አንዱ የሚያበለጽጉ ወዳጅነቶችን ማስቀጠል እና ማጠናከር አለመቻል ናቸው። ከወዳጆች ለረዥም ጊዜ መነጠል የሚያልቅ ነዳጅ ወይም ባትሪ ያለው መኪናን ይዞ ደግሜ ነዳጅ አልቀዳም ወይም ቻርጅ አላደርግም እንደማለት ነው። የቱንም ያክል የጉዞው መጀመሪያ ላይ ታንኩ ቢሞላም ሆነ ባትሪው ቻርጅ ቢደረግም ቸል ሊባል አይገባም። እንደውም ከተለመደው በተለየ መልኩ በተጠቀምነው ቁጥር ዐይኖቻችን በአስተውሎት ጌጁን መመልከት አለባቸው። ይኽን ካላደረግንሳ? እርዳታ የሌለበት ቦታ ድንገት ልንቆም ሁሉ እንችላለን።
የወዳጅነት ትሥሥር ለምን ያስፈልጋል? ከወዳጅነት ያነሱ ውሎዎች ተመሳሳይ ጥቅም የላቸውም? የሚያስፈልገን ሰው እንጂ የቅርብ ሰው የግድ መሆን አለበትን? መልሱ ግልጽ ነው፤ ወዳጅነት በምንም አይተካም። የሚያስፈልገን ሰው ብቻ ሳይሆን የቅርብ ሰው ነው። የዚህ ማሳያውም ከብዙ ሰዎች ጋር ውለን ማንንም ያላገኘን ያህል ይሰማናል፤ ከአንድ ሰው ጋር ውለንም ዓለም ሁሉ ከእኛ ጋር የዋለ ይመስለናል። ወዳጆቻችን በእርግጥም ዓለሞቻችን ናቸው።
ወዳጅነት ከርዕሰ ዜናዎች ያለፉ ውስጣዊ ጉዳዮች የሚወሩባቸው የተለዩ እና የከበሩ ስፍራዎች ናቸው። በወዳጅነት ውስጥ ዋንኛው ጉዳይ ነገሮች እና ሌሎች ሳይሆኑ እኛው ራሳችን ነን። ስሜታችን፣ ህልማችን፣ ፍርሀታችን ሆነ ተስፋዎቻችን ያለ ስጋት ይገለጻሉ። ራሳችንን አንዳችንን በሌላው ፊት ማራቆትም አይቸግረንም። እንዲህ ዐይነቶቹ የወዳጅነት ግንኙነቶቹ ያበለጽጉናል፤ ከምንም በላይ ብቸኝነት አይሰማንም፤ አብሮነታችንም ያበረታናል።
ወዳጆችን ማጣት በእርግጥም አቅም አልባ ያደርጋል። ወዳጅነቱ ከሰው ጋር ብቻም አይደለም፤ ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነትንም ጭምር ያጠቃልላል። የምንቀርበውን አምላክን በመራቅ እንከስራለን። ለመጸለይ፣ ለማሰላሰል፣ እና ለአብሮነት ደግሞ የጥሞና፣ ያሰላስሎ እና የህብረት ጊዜ ያስፈልጋል።
የተለወጥኩባቸውን ቀኖቼን ሳስባቸው ሌላው የተገነዘብኩት ነገር ራሴን መዘንጋቴም ነበር። ከእንቅልፌ ባሻገር በየቀኑ ለራሴ ብዬ የምመድባቸው ሰዓትት እየቀነሱ ነበር፤ ለራሴ ሆን ብዬ ጊዜ የመስጠቱ ልማዴም እየተወሰደብኝ ነበር። ከእንቅልፍ ከተነሳሁበት እስክተኛበት ያሉትን ሰዓታት ስሾር አገኛለሁኝ። ከአንዱ ነገር ቀጥሎ የሚሰራ ሌላ ነገር ይታየኛል፤ በጎደለው ሁሉ መቆምም እሻለሁ፤ አንዳንዴም ሰዋዊው ውስንነቴም የጠፋብኝ ሁሉ ይመስላል።
በባተሌነቴ ውስጥም ራሴነ ሳልሞላ በመስጠት ላይ ብቻ ስለተሰማራሁ ለሌላውም የምፈልገውን ያክል የምጠቅም ሆኜ መቀጠል አለመቻሌም በሂደት ግልጽ ሆኖልኛል። ሳስተውልም እኔኑ ብቻ ደስ የሚያሰኙኝን ነገሮች በሙሉ ከሕይወቴ እየቀነስኳቸሁ ለሌላው ወደመኖር እያዘነበልኩ ነበር። የኔኑ ደስታ እና ትርጉሞች አሳንሼ ለሌላው ደስታ እና ትርጉም ብቻ መቃኘቴ ችግር ነው። እንዲህ ዓይነቱ ቅኝት መንፈሳዊነት ቢመስልም በፍጹም መንፈሳዊነት አይደለም።
የአገልግሎታችን መጨረሻውም በምንም መልኩ ራስን መጣል ሊሆን አይችልም። እንዲህ ተቃኝቼ ታዲያ እንዴት አልደክም? እንዴትስ አቅም አልጣ? ስለሌላው ስጠነቀቅ ለካ ራሴን ዘንግቼዋለሁኝ። ራሴን መርሳትና ሌሎችን ብቻ ማሰቡም በእርግጥም ሌላኛው ችግሬ ነበር።
እናሳ?
መቋጫዬ ግልጽ ነው። ያለ ሥሥት ለመስጠት መፈለጌ ችግር አይደለም፤ ይህንኑ ምኞት አምላክ በውስጤ ስላስቀመጠም አመስጋኝ ነኝ፤ እንኳንም ያለ ሥሥት መስጠት የሚፈልግ ሰው ሆንኩኝ። እንኳንም ሁሉ ነገር በኔ ዛቢያ ብቻ ይሽከርከር አላልኩም። ዐይነተኛው ችግሬ ራሴን መንከባከብ መዘንጋቴ ነው፤ መስጠት መተካት መፈለጉን መርሳቴ ዋጋ አስከፍሎኛል። ሳልተካ መስጠቴን ካላስተካከልኩም ባዶነቴን መስጠት መጀመሬ አይቀርም፤ ባዶነቴ ደግሞ ሌላውን ቢያሳዝን እንጂ አይጠቅምም፤ ስጦታዬንም ጉዳት ያደርገዋል፤ ከባዶነቴ ለመስጠት በሞከርኩ ቁጥርም ሌሎችን በእርግጥም እጎዳለሁ። ስለዚህም የሚሻለኝ ሁል ጊዜ ያወጣሁትን መተካት ነው። መተኪያ መንገዶችም የልብ ለልብ ወዳጅነቶቼን ማስቀጠል እና ራሴን መንከባከብ መቻል ናቸው።
Written by : Dr. Tekalign Nega
Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.
Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.


Enlightening !!! God bless you!
It is a a great message. It helped me see myself and take time to rest and gain what I lost. God bless you!