
ደስታን መካፈል
በዶ/ር ተካልኝ ነጋ አንጎሬ
ሕይወት መልከ ብዙ ናት። እንደምታስከፋን ሁሉ ታስፈነጥዘናለችም። ደስታችንም እኛ ጋር ብቻ እንዲቀር ስለማንፈልግ የደስታ መሰባሰብን ከጉድለታችን ጭምር እናቅዳለን። ለቅርቦቻችን እየደወልንም ኑ አብረን ሀሴትን እናድርግ እንላለን። ለቅርቦቻችን የደወልነው አንዳንዱ የስልክ ጥሪ ግን ያልጠበቅነውን ይዞብን ይመጣል። ደስታችሁን እንዲጋራ በሚል የደወልንለት የቅርባችን ሰው ደርሶ “በቅድሚያ መነጋገር አለብን” ይለናል። የዚህ መጣጥፍ አላማም ይህንን ተከትሎ የሚሰማንን ስሜት እና ነገሩን መፈተሽ ነው።
አብሬህ ደስታህን ከመቋደሴ በፊት በቅድሚያ እንነጋገር የሚለን ወዳጅ ምን ዐይነት ስሜት እና ጥያቄ ይፈጥርብናል? በእርግጠኝነት ስሜታችሁ ከደስተኛነት ጥግ ወደ ሀዘን ጥግ በሰከንዶች ፍጥነት ይለጋል፤ የተፍታታው ሰውነታችሁም ውጥር ይላል፤ ጥያቄዎችም ይግተለተላሉ። ለደስታ ግብዣችን የተሰጠን እንግዳ ምላሽም ስሜታችንን እና ሰውነታችንን ቢለዋውጠውም በእርግጥም አይገርምም።
መቼም ሰው ደስታችሁን ለመጋራት ቅድመ ሁኔታ ካስቀመጠ የሆነ ጥሩ ያልሆነ ነገር መኖሩ ግልጽ ነው። ጠንከር ያለ እና የተካረረ ነገር ከሌላኛው ወገን እንዳለም ይገባናል። በብዙ ብስለት፣ ንዴታችንን ተቆጣጥረን፣ ስልካችንን ብንዘጋውም ነገሩ ስልኩ ከተዘጋም በኋላ እኛ ውስጥ ይቀጥላል። ስልካችሁን ካስቀመጥን በኋላም ነገሩ ከመረሳት ይልቅ የሚከነክን እና የሚያብከነክን ጉዳይ ይሆናል፤ በርካታ ጥያቄዎችም ያለከልካይ ይግተለተላሉ።
በመካከላችን መፈታት ያለበት ጥያቄ ቢኖርስ ጊዜው አሁን ነውን? ደስታዬን ለመጋራት የቀደሙት መልካም ትዝታዎች ብቻቸውን አይበቁምን? መገናኘቱ የተፈለገውስ ለምንድን ነው? ለመወያየት ወይም ለመክሰስ? ሳላውቀው ጥፋተኛ እና ተበዳይ ተደርጌ ተስያለሁኝን ማለት ነውን? ከሆነስ ለምን እስከአሁን ድረስ ተጠበቀ? ነገሩ ይህን ያክል ልብ ውስጥ ከከበደ ለምን ቀዳሚ አልተሆነም? እኔ ባልደውል ኖሮስ? የእኔ አተያይ እና ህመምስ አንዳች ቦታ አልተሰጠውም ማለት ነው? እኔ እንደ በዳይ እርሱ ደግሞ ተበዳይ ሆነን ተፈርጀናል ማለት ነው? የምንገናኘውም እኔን ለመኮነን እና ራስን ለማጽደቅ ነውን? ነገሩ ታግሼ መተዌ እንደጥፋት ተቆጠረብኝ ማለት ነውን?
እኚህን እና መሰል ጥያቄዎች ባብሰለሰላችሁ ቁጥርም ልባችሁ እየሻከረ፣ እንዳልተፈለጋችሁ እየተሰማችሁ፣ ለግንኙነታችሁ እኩል ዋጋ ትሰጡ እንዳልተነበረ ይሰማችሁ ይጀምራል። ላፍታ ከመብሰልሰላችን ወጥተን ዋናውን ነገር ዋና እናድርግ። በሌላው ሰው ደስታ ለመደሰት ግን ቅድመ ሁኔታ ከቶውን ያስፈልጋልን? እንኳንስ የሆነ ጊዜ ጥሩ ትውስታ የነበረንን ሰው ይቅርና በክፉ የሚያስበንን ሰው ደስታ ልንካፈል አንችልምን? የደረሰብን ነገር የቱንም ያክል ክፉ ቢሆንም በሌላው ሰው ውስጥ የምናየውን አምላካዊ ቸርነት በቅንነት ከመመልከት መቼም ቢሆን መጉደል የለብንም።
የቱንም ያክል እንደተበደልን ቢሰማንም ልባችን የቀድሞ ወዳጃችንን ውድቀት መጠበቅ የለበትም፤ የወዳጃችን ክፉ ነገርም መቼም የደስታችን ምንጭ ሊሆንም አይገባል። ይህንን የተገነዘበው ጠቢቡ (ምሳሌ 24፡17) “ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ፥ በመሰናከሉም ልብህ ሐሤት አያድርግ።” ሲል ይመክረናል። ምክሩም ሌላው ሰው ክፉ አድርጎብን ቢሆን እንኳ ክፉውን ማሰብ የሰውነት ልክ አለመሆኑን ያሳስበናል። ዐይን ስለ ዐይን በሚል ሕግ ዘመን የኖሩ ይህን ያክል ከተጠበቡ፣ ጠላትህ ቢራብ አብላው እና ጠላትህን ውደድ በሚል የፍቅር ሕግ እንዲኖሩ የተጠሩ እንዴት በበጎነት ይበልጥ መጠበብ አይኖርባቸውም። በመጎዳታችን ሀዘን መካከል እንኳ የሚጠላን ሰው ደስታው ደስታችን ሊሆን ይችላል፤ ይገባል።
በደስታ ግብዣ መካከል የእኛን ደስታ በአብሮነት ለመካፈል አለመፈለግን መግለጽ የጋባዡን ሥነ ልቦና እጅግ ይጎዳዋል። ለካ ክፉ ነገር እንዲገጥመኝ እየተጠበቀ ነበርን የሚል ደስ የማይል ስሜት እንዲፈጠርብንም ያደርጋል። ከዚህ ቀደም የቱንም ያክል ምቹ ቀን ወዳጃችን እየጠበቀ ቢሆንም እንኳ፣ በደስታችን ቀን በድለኽኛልና ደስታህን እንድንካፈል ሳታውቀው ስመዘግበው የነበረውን የበደል ዕዳህን ክፈል መባል ሆኖ ይታየናል። በደስታችን ቀን የክስ ዶሴው መመዘዙም ይበልጡኑ ያሳምመናል። ወዳጃችን በደስታችን ቀን በደለኛነታችንን ማንሳቱ እና እኛን የወቀሳ ማዕከል ማድረግ መፈለጉ ያበሳጨናል።
ሰከን ብለን ስናየው ግን ደስታችንን ለመካፈል ቀድመህ የበደል ዕዳህን አወዳድቅ የሚሉን ወዳጆቻችን ሁሌም ሁሉ ነገር በእኛ ዙሪያ መንቀሳቀስ አለበት በሚል አባዜ መያዛቸውን ያመለክታል። እንዲህ የማያምኑ ከሆኑ ደግሞ ደስታችንን መካፈል ባልቸገራቸውም ነበር። ተበድሎም እኮ የሌላውን ደስታ ማጣጣም ይቻላል፤ የሚፈለገውም ጥቂት ቅንነት ብቻ ነው። የደስታዬ ጥሪም እግዚአብሔር ደግስ አይደለምን ከቸርነቱ ሁሉን ያጠግባል በሚል የብስለት ቅኔን ለአምላክ ጭምር መቃኘት እንድንችል አቅምም ይሰጠናል። ይህን አቅም ከማንም ሰው ጋር ባለን መልካም ግንኙነት ውስጥ ካጣነው ግን ልባችን ለእኛም የማይጠቅም መራርነት አለበት እና ፈውስ ያሻዋል።
እንደተበደልን በብዙ ምክንያት ሊሰማን ይችላል። አንዳንዴ መበደላችንም በእኛ ዐይን፣ በሌሎች ዐይን ሆነ በአምላክ ዐይን ፊትም ልክም ሊሆን ይችላል። ተበድለናል ማለት ግን ከሌላኛው ጋር አብረን የምንቀመጠው ለመክሰስ ነው ማለት አይደለም። የንግግራችን መነሾ ሆነ ድምዳሜ ሌላኛውን ማሳጣት ግን መቼም ሊሆን አይገባም። የምንገናኘው ሆነ የምንነጋገረው ለግንኙነቶቻችን ካለን ከፍ ያለ ቦታ መጀመር አለበት፤ ለሌላኛው ሰው ያለን አክብሮት ከክስተቶች የተነሳ ጥያቄ ውስጥ ቢገባም አክብሮታችንን ሆነ ልባችን ውስጥ ከዚህ ቀደም ያ ሰው ያገኘውን ቦታ በመካድም መጀመር የለብንም። ስለዚም መገናኘታችንን ስናስብ የምንመጣው በልበ ሰፊነት ለማዳመጥ እና የእኛን አተያይ እና የተሰማንን ስሜት ለመግለጽ መሆን አለበት፤ የእንነጋገር ጥሪ ከልናገር ይልቅ ላድምጥ የሚለው ቅኝት ሊጎላበት ይገባል።
ከውይይታችን በፊት የእኛን ጻድቅነት ወስነን፣ ይቅርታን ለመቀበል ብቻ ተዘጋጅተን፣ ሌላኛውን ኮንነን ከመጣንስ? ነገሩ አሳ ጎርጓሪ መሆኑ አይቀርም። እኛ የረሳናቸው እና በሌሎች በይቅርታ የተዘጉ ዶሴዎች መልሰው ይከፈታሉ። ይህ እንዳይሆን ግን ማናችንም በሁሉም ጉዳይ ጻድቅ አለመሆናችንን አንዘንጋ። ሰው ስለሆንን ከበደልነው ይልቅ የበደልነውን ማስታወስ እንደሚገንብን አይጥፋን። በሁሉ ነገር ውስጥ ሁሌ ጻድቅ ነን የሚል የልጆች ጫወታ ስለማይጠቅምም ይቅርብን። ስለዚህም መገናኘት የምንናፍቀው ለመነጋገር እንጂ ለመክሰስ ከቶውንም አይሁን። አለበለዚያ ግን የአላዋቂ ሳሚ ነገር ይሆንብናል፤ በንግግራችን ሌላ ቅያሜ እንፈጥር ይሆናል እንጂ የተበላሸውን አናድስም።
አንዳችን ሌላችንን በድለን ስንገኝም ማዕከሉ ግንኙነታችን ይሁን እንጂ ማዕከሉ እኔነት አይሁን። ግንኙነታችን እኔ ከምንለው ፍላጎት በላቀ ቁጥር ይቅርታ መቀበልም ሆነ መስጠት ይቀለናል። ለግንኙነታችን ልባችን ዋጋ ካልሰጠስ? ግንኙነታችን የምንፈልገው ለታይታ እና ለይስሙላ ነውና ሁሉ ነገር ትወና ይሆናል፤ እንጎዳዳ እንጂ አንተናነጽበትም። ትወና ደግሞ በሚቀራረቡ ሰዎች መካከል መቼም አያዋጣም፤ ደስም አይልም። ወዳጅነት እና ቅርርብስ በዚህ አስመሳይ ዓለም ውስጥ እውነተኛነት መፈለግ አይደለምን? አንዳችን ለሌላችን አለንለት የሚል ቅርርቦቻችን ካልፈጠሩስ ምን ይረቡናል? አንዳችን ለሌላችን አለን የሚለው አብሮነት ከሌለም ግንኙነታችን ጥቅም ተኮር እና የይስሙላ ይሆናል፤ እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት ደግሞ የትም በሽ ነውና የሚናፈቅ አይደለም። እውነቱን ከተነጋገርንም እንዲህ ዐይነቶቹ ግንኙነቶች ይጨንቃሉ።
ግንኙነታችን ከግላዊ ፍላጎታችን ባሻገር በልባችን ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ሲያገኝስ? ግጭት አያስደነግጠንም። መነጋገርን የምንፈልገውም ሌላውን በማድመጥ እና በመረዳት ውስጥ የጋራ ፈውስ እንዳለ ስለምናምን ነው። ስለዚህም አዳማጭነታችንም ከተናጋሪነታችን ይልቅም ይጎላል። ይህ እምነታችንም ማንንም ከመክሰሳችን በፊት የምናደምጥበት መድረክ እንድንናፍቅ ያደርገናል። ስሜታችን መጎዳቱን ሳንክድም ርሁሩህ መሆንም አንችላለን። ሳንጠየቅም ጭምር ለሌላው ይቅርታ መስጠት የምንችልበት አቅምም ይኖረናል።
መነጋገርን የምንናፍቀው የታመቀውን አፈንድተነው እንደ ፍጥርጥሩ ይሁን ለማለት አይደለም። የሚገዛን ፍላጎት ግንኙነታችንን ማደስ እንጂ አንዳችን ሌላችንን ማብጠልጠል ወይም ማሳጣት አይደለም። ከሌላው ጋር ያለን ግንኙነት ቅኝቱ መካሰስ ከሆነስ? ቀስ በቀስ አዎንታዊነታችንን እየቀነሰ፣ ግንኙነት የሚፈልገው ስሜታዊ፣ አካላዊ እና አእምሮዋዊ ጥንካሬም እየተሰለበ ይመጣል። አንዳችንም በሌላችን ላይ ያለንም እምነት ይቀንሳል። መተማመን ሲቀንስ ደግሞ እውነተኛ ማንነቶቻችንን መደባበቅ እንጀምራለን። ይህንን ልብ ባልን ቀንም ምናልባትም ለግንኙነቱ ያለን ዋጋ አንድ ዓይነት አይደለምና ግንኙነቶቻችንን መልሰን ብንፈትሽ እና ተገቢውን ድንበር ብናበጅ መጎዳዳታችንንም ብንቀንስ መልካም ነው።
Written by : Dr. Tekalign Nega
Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.
Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.


Nice Article