ውይይት ወይስ ክርክር? በዘመነ ማኅበራዊ ሚዲያ

በዶ/ር ተካልኝ ነጋ አንጎሬ

1.ችግሩን መፈተሽ

በማኅበራዊ ሚዲያዎቻችን ላይ በርካታ ሥነ-መለኮታዊ ይዘት ያላቸው ጉዳዮች በአማኞች መካከል ይንሸራሸራሉ። እነዚህን ጉዳዮች ተከትሎም ሰዎች በብርሀን ፍጥነት ይቧደናሉ፤ ጣታቸውንም እርስበርስ ይቀሳሰራሉ። ነገሮችም እያደር እየተወሳሰቡ ይሄዳሉ፤ ብዙም ሳይቆይ አንዳችን የሌላችንን ድምጽ ማድመጥ የሚያቅተን ደረጃ እንደርሳለን።

ከእኛ የተለየ አቋም ያላቸውን ሰዎችስ እንዴት እንመለከታለን? በእውነት ላይ ሆን ብለው ያደቡ አድርገን መፈረጅ እንጀምራለን። ልዩነቱ በአብዛኛው የአመለካከት ብቻ መሆኑን በመዘንጋት እራሳችንን በጦርነት ውስጥ እንዳለን እንቆጥራለን። በዚህም የተነሳ ሌላው ሰው ሊሰማ የማይገባው፣ ይባስ ብሎ ደግሞ በእኛ ክልል ፈጽሞ ሊሰማ የማይገባው ድምጽ ተደርጎ ይፈረጃል።

የምንነጋገርበት መንፈስና ቋንቋ ቀስ በቀስ ይለወጣል። የራሳችን ስህተቶች ችላ ሲባሉ የሌላው ድካም ግን ይጋነናል። ሌላው ትክክል ቢሆንም እንኳ ቅንነቱና ገፊ ምክንያቱ ይጠረጠራል፤ ስብዕናው ይጠቃል፤ ማንነቱም ይብጠለጠላል። በሂደት ርዕሰ ጉዳዩ ራሱ ጠፍቶ እኛው ግለሰቦች ርዕስ እንሆናለን። ሌላውን ማሳጣትም ዋነኛ ግባችን ይሆናል። ራሳችንን የእውነት ጠበቃ አድርገን ስንመለከት፣ ሌሎችን የእውነት አጥፊዎች ወይም ‘አመቻማቾች’ ብለን እንፈርጃለን። ሌላውን የምንገልጽበት መንገድም ጭካኔ ይጎላበታል።

ብዙም ሳይቆይ “ስለ እውነት” ብለን አንዳችን ከሌላችን መለየትን እንሻለን፤ ሌሎችም እንዲለያዩ እናነሳሳለን። ከልዩነታችን ጋር አብረን እንኑር የሚሉ ድምጾችንም ‘አመቻቾች’ በማለት እንዘምትባቸዋለን። አንዳችን የሌለንበትን ተቋም ማቋቋምም የንጽሕናችን ማስጠበቂያ ይመስለናል።

ይህ ሁሉ ሂደት ከውይይት ወጥተን ወደ ክርክር ጎዳና እየገባን መሆኑን ያሳያል። ተከራካሪዎቹ ግን የዚህን ሂደት ፍጻሜና ትልቁን ምስል የምንዘነጋ ይመስለናል። ብዙ ነገርን ከሥረ መሰረቱ እየነቀነቅን መሆናችንን አናስተውልም። ነገሩን የሚመለከቱ አማኞች “አማኝነት እንዲህ ከሆነ ምን ይፈይድልኛል?” የሚል አስተሳሰብ ማጎልበታቸውን እንዘነጋለን። የራሳችን ሚዛን መሳትና አክራሪነትም ተአማኒነታችንን አደጋ ውስጥ እንደምንጥለው አይገባንም።

2. ክርክር ወይስ ውይይት?

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምሁር የሆኑት ማርቲን ማርቲ፣ ውይይት እና ክርክርን በግልጽ ይለዩዋቸዋል። ትኩረታቸውም የተለያየ እንደሆነ ያስረዳሉ። ተወያይ ትኩረቱ በጥያቄው ላይ ሲሆን፣ ተከራካሪው ግን ትኩረቱ በመልሱ ላይ ነው። ይህ ልዩነት የአዕምሮ ቅኝታችንን በእጅጉ ይለውጠዋል።

ተከራካሪ ራሱን እንደ ባለመልስ ይመለከታል። ከእሱ የተለየ መልስ ያለው ሰው መሸነፍ እንዳለበት ያምናል፤ ሌላውንም ወደ ራሱ ሊለውጠው የሚገባው ባለጋራ አድርጎ ያየዋል። ካልተለወጠስ? ለቆምንለት እውነት እንቅፋት ሆኗል ብለን ስለምናስብ ከእኛ እንደ አንዱ መቆጠር ማብቃት እና መወገዝ እንዳለበት እናስባለን።

ተወያይ ግን ትኩረቱ በጥያቄው ላይ ነው። ስለዚህም ሌላውን ሰው በተለየ አተያይ ይመለከተዋል። ከእኛ የተለየ አስተያየት ያለው ሰው ይከበራል፤ እንደ አንዳች ነገር የሚያቀብል ተባባሪም ተደርጎ ይታያል።

3. የአደማመጥ አይነቶች እና የእኛ ዝንባሌ

አዳማጮች ሁሉ አንድ ዓይነት አይደሉም። ልዩነቱም በአደማመጣችን ቅኝት ላይ ነው። የዘርፉ ባለሙያዎች የአደማመጥ ቅኝቶቻችንን ብዙ ቦታ ይከፍሉዋቸዋል። ለዛሬ ግን አንዱን አከፋፈል ወስደን በሥሩ በሚገኙ በአራቱ ዋና ዋና የአደማመጥ አይነቶች ላይ እናተኩራለን።[1]

ሀ. በልማድ መነጽር ማድመጥ

ሰዎች ከቀደሙ ልምምዶቻቸው የተነሳ የልማድ እስረኞች ናቸው። የምናደምጥ ቢመስለንም በእርግጥ  አድማጮች አይደለንም። የሚሰማው ነገር ወደ ውስጣችን የሚዘልቀው ከነበረን እውቀትና እምነት ጋር ሲስማማ ብቻ ሆኖ የሚገኝባቸው ጊዜያት ጥቂት አይደሉም። በቀደመው መረዳታችን መነጽር ለላላፈ ነገር በአብዛኛው ዝግ ነን። ይህ ቅኝት ሌላው ሲናገር እኛን ከራሳችን አመለካከት ጋር ብቻ እንድናነፃፅር ያደርገናል። ትኩረታችን ለሌላው የሰጠን ቢመስልም የትኩረታችን አቅጣጫ ግን እኛው ራሳችን ነን፤ ከውጭ የምናደምጠውም ከእኛው ከውስጣችን ሀሳብ ጋር የተስማማውን ነው፤ የእኛን ሀሳብ ያላስተጋባ እኛ ጋር ቦታ የለውም።

ለ. በተከፈተ አዕምሮ ማድመጥ

አንዳንዶቻችን ከሌሎቻችን የበለጠ አእምሯችን ክፍት ነው። ነገሮችን የምናደምጠው አዲስ ነገር ይገኝበታል በሚል የጉጉት ስሜት ነው። ስለዚህም “ነገር እንዲህ ይሆንን?” በሚል በሚመረምር ቅኝት እናደምጣለን። የሚገርም፣ ያልጠበቅነው እና የሚስብ ነገር ከቀደመው ግንዛቤያችን ጋር ባይገጥምም ትኩረታችንን ይይዛል። ከትዝታችን እንዳያመልጥም በማስታወሻችን ላይ ለመጻፍ ጊዜ እንወስዳለን። ጊዜ ወስደንም ነገሩን ለማሰላሰል፣ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን ለመፈተሽም እንጥራለን።

የዚህ አደማመጥ ጥንካሬው ትኩረቱ ከእኛ ወደ ተናጋሪው መዞሩ ነው። የሚናገረው ሰው በእርግጥም እየተሰማ ነው። ውስንነቱም አደማመጡ አእምሯዊ ብቻ መሆኑ ነው። ካልተጠነቀቅን ፈራጅነታችን ይጎላል፤ አዳዲስ ነገሮችንም ከሩቅ ተኩሰን የምንገድል ልንሆን እንችላለን። ራሳችንን በትህትና አስገዝቶ መስማት ሊቸግረንም ይችላል። የሆነ ነገር እናጣለን የሚለው ፍርሃታችንም ነገሮችን በትክክል እንዳንመዝን እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል።

ሐ. በሌላው ፈንታ ሆኖ ማድመጥ (ርኅራኄ የተሞላበት አደማመጥ)

አብዛኛው ሰው ከራሱ ቦታ አልፎ ሌላውን ከሌላው አንፃር የመመልከት አቅም ይቸገራል። ይህ ዓይነቱ አደማመጥ የሚመነጨው በፍቅር ከሚሰጠን ልበ-ሰፊነት ነው። አደማመጡ አእምሯችንን ብቻ ሳይሆን ልባችንንም የሚያሳትፍ ነው። ርኅራኄም ግንኙነታችንን ይገዛል። ይኽ እንዲሆን ግን የምናዳምጠው ሰው ከምንም በፊት ልባችን ውስጥ ከፍ ያለ የአክብሮት ሥፍራ ማግኘት ይኖርበታል።

መ. ፈጠራ ያለበት አደማመጥ (Generative Listening)

ፈጠራ ያለው አደማመጥ ከምንም በላይ ድፍረትን ይፈልጋል፤ መንገዱም ከባድ ነው። በልባችን ውስጥ ሌላውን ከመረዳት ያለፈ አዲስ ነገር የማዳመጥ ዝግጁነት አለን። ራሳችንንም ከተለየ ሀሳብ ጋር ስንሟገት አናገኘውም። መንገዱ የሚከብድበትም ዋናው ምክንያት ራስን ዝም ማሰኘት ስለሚፈልግ ነው። በዚኽ መንገድ አዳምጠን የቀደመውን እኛን ብቻ ሆነን መቀጠል አንችልም። እያንዳንዱ ውይይትም የሚጨምርልን አዲስ ነገር አለው።

ነገሮችን እንዳሉ ተቀብሎ ለመማር መፍቀድን ስለሚጠይቅ ከልብ ባሻገር ፈቃዳችንንና ውሳኔያችንንም አብሮ ማንቀሳቀስ ይፈልጋል። በዚህ አደማመጥ ስንሰማም ሌላውን ሳይሆን ራሳችንን በተለየ መንገድ እንጠይቃለን፤ እንሞግታለንም። ከብዙዎቹ የሚነሱ ጥያቄዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ እነዚህ ናቸው፦

እኔ ከማስበው የተለየ ነገር የማደምጠው ሰው ያስባል፤ የተለየ ነገር ማሰቡም ችግር አይደለም። ከሀሳብ ልዩነታችን ምን ልቀስም እችላለሁ?

ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ተያይዞ የማደምጠው ሰው ያሉት ቅድመ ዕሳቤዎች እና እምነቶች ምንድን  ናቸው?

እኔ ያላየሁትን የማደምጠው ሰው ግን ሊያያቸው የሚችላቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የእርሱ አተያይ የእኔን አተያይ በምን መልኩስ ያበለጽገዋል?

4. ውስንነታችንን እንዴት እንሻገር?

አብዛኞቻችን ሌላው ሲናገር ዝም ስላልን ብቻ ራሳችንን እንደ ጥሩ አድማጭ እንቆጥራለን። የአደማጭ የመሰልንባቸው እነዚህ የዝምታ ጊዜያት ግን በአብዛኛው ከእኛ የሚለዩ ሀሳቦችን ለመሞገት የምንዘጋጅባቸው የመልስ ምት መዘጋጃ ጊዜያት ናቸው። ይኽ እንዳይሆን ከፈለግን ሌላውን ስናደምጥ “ላቋርጥ፣ ልመልስ እና ልሞግት” የሚለውን ውስጣዊ ድምጽ አደብ ማስገዛት ይኖርብናል።

ብዙዎቻችን ከእኛ የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ሰዎች ሳናደምጣቸውም “ጠንቅቀን እናውቃቸዋለን” ብለን እናስባለን። ቀድመን ከምናውቀው የተለየ አንዳች ነገር እንደማይጨምሩልንም እናምናለን። እንዲህ ዓይነቱ ቅኝት ከቀደመው አስተሳሰባችን ጋር የሚስማሙት ላይ ብቻ ትኩረት እንድናደርግ ገደብ ይሆንብናል። ከዚህ ቅኝት ካልወጣን ግን አንዳች አዲስ ነገር አንማርም።

በሌላው ፈንታ ሆኖ በማዳመጥ የሚገኘውን መረዳትም ከማንፈልገው ሀሳብ ጋር መተባበር መስሎን የምንጨነቅ አለን። አንድን ነገር በትክክል መረዳት ማለት ግን ነገሩን መደገፍ ወይም ማጽደቅ ማለት አይደለም። መረዳት የነገሮችን ውስብስብነት እንድንረዳ አይናችንን ይከፍትልናል፤ በጋራ መፍትሄ ፍለጋ ሂደት ውስጥም አዎንታዊ ሚና የመጫወት አቅም ይፈጥርልናል።

ከክርክር ጎዳና ወጥተን የውይይትን መንገድ የምንከተለው እርስ በርሳችንን በማድመጥ እንደሆነ ልብ እንበል።

[1]  C.OttoScharmer, Theory U: Leading from the future as it emerges  (Berrett-Koehler Publishers, 2009), 11-13.

Share This Story, Choose Your Platform!

Written by : Dr. Tekalign Nega

Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.

Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.

Subscribe To My Page

BE NOTIFIED ABOUT RECENT UPDATES

One Comment

  1. Befikru Shibru August 15, 2025 at 4:34 am - Reply

    Thank you Doc

Leave A Comment