
ስስነት
በዶ/ር ተካልኝ ነጋ አንጎሬ
አንዳንድ ጉዳዮች ለልባችን እጅግ በጣም የቀረቡ ናቸው። ለእነሱ በጣም ስስ ነን። “በእርሱ ጉዳይ አትምጡብን” እንላለን። “በእነዚህ ጉዳዮች አትምጡባቸው” ይባልልናል። ታዲያ ደፍሮ አጥሩን የተላለፈ ሲገኝስ? ከዚህ ቀደም እኛም ሆንን ሌሎች የማናውቀው ደግሞም የማናኮራበት ማንነታችን ከመቅጽበት ይገለጣል። የተገለጠውን አዲሱን ማንነት እኛም ሆንን ሌሎች ባንወደውም ፈጥኖ አደብ ማስገዛትም ያቅተናል።
በአንዳንድ ጉዳዮች መስመሩ ሲታለፍ፣ በዝምታ የምንታወቅ ሰዎች ተናግረን አይወጣልንም። ትዕግስታችን የተጨበጨበለት ቢሆንም በአንዳንድ ጉዳዮች ግንፍሎች ነን፤ በቁጣ ለማንባረቅ ሰከንድ እንኳን አንፈጅም። በብዙ ነገር የምንራራ ሆነን በአንዳንድ ጉዳዮች እንጨክናለን። መስመሩን ተላልፏል የምንለውን ሰው እንደ ጠላት እና ከእኛ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር እንደሌለው አድርገን ለመፈረጅም አናመነታም። ይህ እውነትም “ለምን እንዲህ ተቃኘን?” እና “መፍትሄውስ ምንድን ነው?” የሚለውን ማሰላሰል የግድ ያደርገዋል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ይኸው ነው።
ለምን?
በአንዳንድ ጉዳዮች ድንገት የምንለወጠው እና የማንፈልገውን ማንነት የምንይዘው ለምንድን ነው? ትዕግስታችንስ ለምን በቶሎ ይሟጠጣል? እነርሱን ለነካስ መራራት የሚያቅተንስ ለምንድን ነው? በእነዚህ ጉዳዮች የመጣብንን ሰው ለምን መወገድ እንዳለበት ጠላት አድርገን እንመለከታለን? አራት ምክንያቶችን እንመልከት።
የመጀመሪያው የጉዳዩ ግዝፈት ነው። ጉዳዩ በልባችን ምን ያህል እንደሰረፀ ያሳያል። ቦታ ያልሰጠነው ጉዳይ አያንገበግበንም፤ ራሳችንንም ስንቆጣ አናገኘውም። ለነገሩ የስሜታችን ያህል ዋጋ የምንሰጠውን ነገር የሚጠቁም ሌላ አመላካች ነገር በሕይወታችን ውስጥ የለም። ይህም የስሜት ሕይወታችንን ከሀሳባች ባልተናነስ መከታተልን ተገቢ ያደርገዋል። ያስቆጣን እና ያስፈነደቀን ነገር ስሜት አልባ ከሆነው እና በአመክንዮ ከታጨቀው ትንታኔያችን ይልቅ እውነተኛ ማንነታችንን ማሳየቱን በልባን መቀበል ይገባናል። ስሜታችን በቀላሉ የሚነካበትን ጉዳይ “ቦታ አልሰጠውም” ማለት ራሳችንን መካድ ይሆንብናል እንጂ አይጠቅመንም። ስለዚህም ስሜታችንን መነካት ጉዳዩ በልባችን ያለውን ቦታ አመላካችነቱን እንመን።
ስሜታችን ለጉዳዩ ያለንን ቦታ ያመለክታል ማለት ግን ስሜታችን አይፈተሽ ማለት አይደለም። ስሜታችን በቀላሉ በሚነካባቸው ጉዳዮች በእርግጥ ነገሩ የሰጠነውን ያህል ቦታ ይገባዋል ወይ ብለን ራሳችንን እንፈትሽ። ማን ያውቃል፣ አንዳንዱ የተንገበገብንለት ነገር ቀድሞውንም ያን ያህል ቦታ ልባችን ውስጥ ያልተገባው ሆኖ ሊገኝ ይችላል። በልባችን ቦታ ያገኘ ነገር ሁሉ ላይ መቆጣት እና ማንባረቅም አለብንም ማለት አይደለም። ቁጣችን በራሱ ጽድቅ አለመሆኑንም መቼም መዘንጋት አይገባም። አለመቆጣትም መለዘብ አይምሰለን። ቁጣችን ያስገኝልናል ከምንለው መደመጥ ይልቅ አድማጭነታችን የሌላውን ጆሮ ለዘመናት እንደሚከፍትም አንዘንጋ።
ሁለተኛው ምክንያት ከግብረገባዊ አተያያችን ጋር ይያያዛል። ስሜታችን መነካቱ የሆነው ነገር ልክ አይደለም ብለን በጽኑ ማመናችንን ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው ተመሳሳይ አቋም መያዝ አለበት ብለን ማመናችንንም ያመለክታል። በጉዳዩ ላይ ግራጫ የሚባል ነገር የለም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳችንንም ይጠቁማል። ለእኛ ግልጽ እንደሆነው ለሌሎችም ግልጽ መሆን አለበት የሚል አቋም ይዘናል ማለት ነው። ባይሆንማ ኖሮ በዚህ ልክ ባልተቆጣን እና ባልተናደድን ነበር።
ነገሩ ግብረገባዊ ነው ደግሞ ልክነትን ተላልፏል ብለን ማመናችን በአብዛኛው አሉታዊ ስሜቶቻችን ውስጥ ያለውን ስሜታዊ ወቀሳ ለማስተናገድ ሽፋን ይሰጠናል። “በዚህ ጉዳይ ያልተቆጣን እና ያልተናደድን በምን ጉዳይስ ልንቆጣ እና ልንናደድ ነው?” በማለት ራሳችንን እናጸድቃለን። ይህንን መታገስም ማመቻመች እንደሆነ ይሰማናል።
ቆም ብለን ማሰብ ከጀመርን ግን ሰከን ማለት እንችላለን። አንድ ነገር ግልጽ ሆኖ ይታየናል ማለት ግን በእርግጥም ለሁሉም ሰው ግልጽ ነው ማለት አይደለም። ለእኛ ግልጽ መስሎን እያለ ለሌሎች ግልጽ የማይሆንበትም ዕድል ይኖራል። ስለዚህም ግብረገባዊ አቋማችንን መልሰን እንፈትሽ። ተላላፊ ላልናቸውም ዕይታችንን እናጋራ፤ እርስ በእርሳችን እንሞራረድ፤ ተፈትነው ያለፉትን አቋሞቻችንን በጽናት እንያዝ።
ሦስተኛው፣ ዋጋ የምንሰጠው ነገር ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል ብለን ማመናችንን ስስነታችን ያመለክታል። ምላሻችን ትልቅ ዋጋ የምንሰጠውን ነገር ለመከላከል የምናደርገውን ጥረት ያሳያል። ስጋት ደግሞ ባህሪው ይታወቃል፤ ቅኝታችን ወደ መከላከል እና ወደ ማጥቃት እነደያዘነብል ያደርገናል እንጂ ከሌሎች ጋር ተባባሪ አያደርገንም። በእርግጥ የምንወደው ነገር የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል? ስጋቱን አጋነን ይሆን? ስጋታችን ከሌላው ጥፋት ይልቅ የእኛን ውስጣዊ የመተማመን ማጣት የሚያመለክት ይሆን? እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳት መቻል ስጋቱን በተገቢው መልኩ እንድንለካ እና ምላሻችንንም እንድንመጥን ያደርገናል።
አራተኛው ምክንያት መተላለፉን ያለማወቅ ጥፋት ወይም ስህተት ብቻ አድርገን አለመመልከታችንን ያሳያል። ጥፋቱን የአጥፊው ማንነት አድርገን ተመልክተናል ማለት ነው። ጥፋት የአጥፊው ማንነት አካል ተደርጎ ሲወሰድ ደግሞ አጥፊውን እንደ ጠላት የመመልከት ዕድላችን ይሰፋል።
በጥንቃቄ ካሰብነው ግን በጥፋት ልክ ሌላውን መበየን ግን መቼም ቢሆን ትክክል አይደለም። መቼም ቢሆን አጥፊው ከጥፋቱ ዋጋው ይበልጣል። ምናልባት ውስን በሆኑ ጉዳዮች ላይ በእርግጥ ለደህንነታችን ስጋት ሆኖ ከታየን ግልጽ እና የማይታለፍ መስመር ማበጀት እንጂ እንደ ጠላት መተያየት አይገባም።
ምን ይሻላል?
ከሌላው ጋር በመሠረታዊ ጉዳዮች ሳይስማሙ እና በጉዳዩ ላይ ባለው አቋምም ሳያመቻምቹ መቆም ይቻላል? ከተቻለስ መንገዱ ምን ዓይነት ነው? መንገዱ ግለታችንን እና መሰጠታችንን ከማይመስሉን ሰዎች ማዳመጥ ጋር ማመጣጠን ነው።
ብዙዎቻችን ከልባችን በተሰጠንበት ጉዳይ እና በምንገበገብለት ነገር ላይ አድማጭነት ይጎድለናል። ግን ለምን? ምናልባት የተለየ ነገር ማዳመጥ መሰጠታችንን እና ስሜታዊ ግለታችንን የሚያጠፋብን ሳይመስለን አንቀርም። ማዳመጥ የሚቀይረን ይመስለናልና ማዳመጥን እንሸሸዋለን። ባለማዳመጥ የምንከላከለው መሰጠት እና ግለት ግን አንዳች አይረባንም፤ በእሳት ተፈትኖ ያላለፈ ነገርንም ወርቅ አድርጎ መቁጠር ራስን ማታለል እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም።
መቼም ቢሆን እንዴት እንደምናዳምጥ እንጠንቀቅ እንጂ ከማዳመጥ አንታቀብ። ማዳመጥ አቋማችንን ደግመን ደጋግመን ለመፈተሽ፣ ለማጠናከር ደግሞም ሲያስፈልግ ለመቀየር የተዋጣለት መንገድ መሆኑን ለአፍታም አንዘንጋ። ሰውነታችንን በእርግጥም ከተቀበልንም ለውጥንም የእኛነታችን አካል አድርገን መመልከት ይኖርብናል። “አይለወጥም” በሚል መወደስ ለሰው የድካም መገለጫ እንጂ ጥንካሬ አለመሆኑንም እናስታውስ።
አንድ ነገር መሠረታዊ እና ዋነኛችን ነው ማለት ከፍተሻ ውጭ ይሁን ማለት አለመሆኑን ብናስታውስ እንጠቀማለን። ለእኛ መሠረታዊ የሆነ ነገር ሁሉ ሁሌ ለሌሎች መሠረታዊ መሆን አለበት ማለትም አይደለም። የነገር ልክነት ሚዛን እንደ አየር ንብረት በፍጥነት ተቀያያሪ ባይሆንም፣ አተያያችን ፍጹም ባለመሆኑ ሊያድግ እና ሊለወጥ ይችላል። ለዚህ እውነትም ምስክር መጥራት አያስፈልግም።
ስንቶቻችን የድሮውን ማንነታችንን በስንት ጉዳዮች ላይ አሁንም ይዘናል? ማናችንም በሁሉም ጉዳይ በድሮ እምነታችን አልቀጠልንም። “በምንም ጉዳይ ላይ አቋሜን አልቀየርኩም” ማለት “ፍጹም ነኝ” ከማለት አይተናነስም። ሰምተንም፣ አስተያየቱ ተገቢ ሆኖ ካላገኘነውም፣ በአቋማችን መቀጠል እየተቻለ “አላዳምጥም” ምን አመጣው? ልክ አይደለም ብለን የምናምነውን ነገር የተላለፉ ሁሉን እንደ ችግር መመልከት አይጠቅመንም።
በጥልቀት ሳናዳምጥ፣ ራሳችንን በሌላው ጫማ ሳናስቀምጥ የምንደርስበት ድምዳሜም “ሰውን ሁሉ እኔን ይምሰል” ከሚል ከንቱ ምኞት ተለይቶ አይታይም። ማዳመጥ የሌላውን “ሌላነት” እንድንገነዘብ ስለሚያደርገን ርኅሩኅ ያደርገናል። ተቃውሞአችንም ሌላኛውን ሳናጠቃ እና ሳንፈርድ እንድንቀርበው ያግዘናል። የሌላውን አንድ ስህተት ወይም ከእኛ የተለየ ፍርድ ብቸኛ ማንነቱ አድርገን እንዳንፈርድ ያግዘናል። የእኛ አተያይም የሁሉ ነገር ሚዛን ይሁን ከማለትም እንታቀባለን።
Written by : Dr. Tekalign Nega
Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.
Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.

