
የሚጎዱ ህብረቶች
በዶ/ር ተካልኝ ነጋ አንጎሬ
ሁልጊዜ አጥፊዎቹ እናንተ ብቻ ተደርጋችሁ መሳላችሁ ምቾት ይነሳችሁ ጀምሯል? ግንኙነቶቻችሁ እናንተን ከማበልጸግ ይልቅ ስለራሳችሁ ያላችሁ መረዳት አሉታዊ እንዲሆን ሚና እየተጫወቱ ነው? “እኔ እንደዚህ ዓይነት ሰው ነኝ?” በሚል ጥርጥር ራሳችሁንስ ከዚህ በፊት አድርጋችሁ በማታውቁት መልኩ እንደገና መመዘን ጀምራችኋል? እነሱ እንደተሳሳቱ እርግጠኛ እየሆናችሁ፣ ሁል ጊዜ እንደ በዳይ ይቅርታ መጠየቅ እየሰለቻችሁ ነው?
ከላይ ለተነሱት ጥያቄዎች መልሶቻችሁ “አዎን” ከሆኑ፣ ይህ በማያበለጽጉ ግንኙነቶች ውስጥ የመኖራችሁ ማሳያ ነው። እነዚህን ግንኙነቶች ያለ አንዳች ማስተካከያ ማስቀጠል ስሜታዊ ጤንነታችሁን ይጎዳል። ስሜታዊ ጤንነታችሁ እንዲጠበቅ ከፈለጋችሁም፣ እነዚህን ቅርርቦቻችሁን በአዲስ አተያይ መመዘን ይኖርባችኋል። በዚህ መጣጥፍም ማያበለጽጉ ግንኙነቶች እንዳይጎዱን ራሳችንን እንዴት መከላከል እንደምንችል እናሰላስላለን።
እየበለጸግን ነውን?
የቅርብ ግንኙነቶች በባህሪያቸው ያሳሳሉ። ሁልጊዜም አብረውን ቢዘልቁ እጅግ ደስ ይለናል። አንዳንዶቹ ቤተሰባዊ ናቸው፤ ከእናት፣ ከአባት፣ ከእህት፣ ከወንድሞቻችን እና ከሌሎች የሥጋ ዘመዶቻችን ጋር ያሉን ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ የሥራ፣ የጓደኝነት ወይም የጉርብትና ሊሆኑ ይችላሉ። የግንኙነት ዓይነት የትኛውም ቢሆንም፣ አብረናቸው በመስጠት እንድንቀጥል ከተፈለገ መመዘን ይኖርባቸዋል። ሚዛኑም “ግንኙነቶቻችን ምን ያህል ሁላችንንም እያበለጸጉን ነው?” በሚለው ላይ መመሥረት አለበት።
በግንኙነቶቻችን ውስጥ በለጸግን የሚባለው ግን መቼ ነው? መልሱ ግልጽ ነው። ግንኙነቶቻችን ሲገነቡን ነው፤ ግንኙነታችን እኛነታችንን እያፈረሱት አበለጸጉን ሊባሉ አይችሉም። ግንኙነቶቻችን የሚያበለጽጉን ተገቢውን የሰውነት ዋጋ ሲሰጡን ነው፤ ግንኙነቶች እያቃለሉን እና እያራከሱን ግን አበለጸጉን ሊባሉ አይችሉም።
ግንኙነቶቻችን አበለጸጉን የሚባሉት በእኛ ውስጥ ያለውን መልካምነት እና አቅም በበጎ ማጎልበት ሲችሉ ነው። ግንኙነቶቻችን ህልሞቻችንን እየገደሉ እና የአቅመ ቢስነት ስሜትን እየፈጠሩ ከሆነም አበልጻጊ ሊባሉ አይችሉም። አበልጻጊ ግንኙነቶች ብቻችንን መሆን የማንችለውን እኛነታችንን በአብሮነት ውስጥ መሆን የምንችልበት ተጨማሪ ዕድል እና አቅም ሊያጎናጽፉን ይገባል። የጠቀስናቸው ባህርያት ያሏቸው ግንኙነቶች ካሉን እሰየው ነው፤ እነዚህንም ልክ እንደ ዓይናችን ብሌን በጥንቃቄ ልንጠብቃቸው ይገባል።
ሁሉም ግንኙነቶቻችን ግን አበልጻጊዎች አይደሉም፤ አንዳንዶቹ በእርግጥም አፍራሽ ናቸው። አንዳንድ ግንኙነቶቻችን የእኛን ልዕልና በመካድ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ እያለን እንዘነጋለን፤ ችላ እንባላለን፤ እነርሱ ወሳኞች እኛ ደግሞ አስፈጻሚዎች እንድንሆን ይጠበቅብናል። ጥረታቸውም የእነርሱን ፍላጎት በእኛ ላይ መጫን እንጂ መሞራረድ አይደለም።
አንዳንዶቹ ደግሞ ስሜቶቻችንን ያለ ርህራሄ በመጉዳት ይታወቃሉ፤ ከረካነው በበለጠ ራሳችንን ተጎድተን እናገኘዋለን። ሌሎቹ ደግሞ ከእኛ ብዙ ጠባቂ፣ ለእኛ ግን ንፉጎች ናቸው። አንድ ቀን ለጥያቄያችን ተገኝተው ሳያውቁ፣ ከሺህ ጥያቄያቸው ውስጥ ያልመለስነውን አንዷን ይዘው ለዘለቄታው ያላዝናሉ። የኛ ፍላጎት አንዴም ቦታ ሳይሰጠው፣ የሌላው ፍላጎት ሁልጊዜ ቅድሚያ ያገኝባቸዋል። ሁሉን ጉዳይ ስለነሱ ስለሚያደርጉት ባዕድነት ይሰማናል፤ ውስጣዊ ደስታችንንም ይመጠምጡታል።
አንዳንዶቹ ከዚህም ይከፋሉ። የምንገናኝባቸውን ቀናት በናፍቆት የምንጠብቃቸው ሳይሆኑ፣ “ምን ይፈጠር ይሆን?” በሚል ስጋት እንድንሞላ የሚያደርጉን ናቸው። ስንገናኝም የክስ ዶሲያቸው እየወፈረ መሄዱን ማወቃችንም የስጋታችን ምንጭ ነው።
መሥመር ማበጀት
ማንኛውም የእርስ በእርስ ግንኙነቶች መርህ አልባ መሆን የለባቸውም፤ መሥመርም ሊሰመርላቸው ይገባል። አካላዊና ስሜታዊ ደህንነታችንን ለመጠበቅ፣ በቀላሉ የማይጣስ ወሰን ማበጀት አስፈላጊ ነው። በግንኙነቶቻችን ውስጥ ምን ዓይነት ባህርያት ተቀባይነት እንዳላቸውና እንደሌላቸው ለሁላችንም በግልጽ ሊታወቅ ይገባል።
እነዚህን ህግጋት አለማወቅ ስሜታችን እንዲጎዳ፣ በራስ ያለን መተማመን እንዲቀንስ፣ እንዲሁም የሌሎች የጥቃት ሰለባ እንድንሆን ያደርገናል። መስመር ማስመር ካልቻልን ደግሞ ላላስፈላጊ ውጥረቶች እንጋለጣለን፤ ፍላጎታችንን ማወቅም ሆነ ማሳወቅ ይቸግረናል፤ ላላስፈላጊ ጥበቃዎች እንጋለጣለን፤ ያለ ጥፋተኝነት ስሜት ለማንፈልገው ነገር “እምቢ” ማለት ይቸግረናል፤ ግለኝነታችንንም ማስጠበቅ ይቸግረናል።
መስመሮቻችንን የምንወስነው ራሳችን መሆናችንንም መገንዘብ ይገባል። “እስከ የት ድረስ ምቾት ይሰማኛል? የቱስ ይረብሸኛል?” የሚለውን የምናውቀው እኛ ነን። ግንኙነቶቻችን ሁልጊዜ ምን ያህል በአክብሮት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን መፈተሽ አለባቸው። ዋጋችንም በትክክል መተመኑ መረጋገጥ አለበት። ሁሉ ነገር ካለቀ በኋላ እንድንሳተፍ ስንጠየቅ፣ ሳንስማማ ዕቅዶች ሲቀየሩ፣ እንዲሁም አክብሮትን የማያሳዩ ተግባራት በተደጋጋሚ ከተፈጸሙ፣ የመሥመር መጣስ ምልክቶች መሆናቸውን ማወቅ ይገባናል።
አብሮነታችን በምንም መልኩ የሥጋት ምንጭ መሆን የለበትም፤ ደህንነትም ሊሰማን ይገባል። በአብሮነት ስም እኛነታችን በተደጋጋሚ ሊጣስ አይገባውም። እንዳይታለፍብን የተናገርናቸው ገደቦች በተደጋጋሚ እንዲጣሱም መፍቀድ የለብንም። እነዚህ መርሆች ሲጣሱ መንቃት ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችንም ማንቃት ያስፈልገናል።
ለራስ መቆም
በእርስ በእርስ ግንኙነቶቻችን ውስጥ ለራሳችን መቆም እንደሚያስፈልገን የማናውቅ ሰዎች ጥቂቶች አይደለንም። ለራስ መቆምም የትህትና መጓደል ወይም ራስ ወዳድነት የሚመስለን አንጠፋም። ከዚህ የተነሳም፣ እጆቻችንን እየጠመዘዙ የራሳቸውን ጉዳይ ማስፈጸሚያ ሲያደርጉን፣ “እምቢ” ማለት የምንችልበትን አቅም እናጣለን። እንድንሻሻል ሳይሆን የበታችነት ስሜት እንዲሰማን በሚል ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ድካማችንን እያነሱ ሲያብጠለጥሉን አናስቆማቸውም። ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት እየተከታተሉ ሲያፈርሱትም ሆነ ስማችንን ሲያጠለሹትም በዝምታ እናልፋቸዋለን።
ግንኙነቶቻችን ለእኛም ሆነ ለሌሎች እንዲጠቅሙ የምንፈልግ ከሆነ ግን ለራሳችን መቆምን መማር አለብን። ለራስ መቆም ግን ምን ማለት ነው? ለራሳችንን ቆምን የምንባለው የእኛን ፍላጎት እና ምርጫ እውቅና ስንሰጥ እና ለሌሎችም ማሳወቅ ስንችል ነው። ለራስ መቆም ማለት ፍላጎታችንን እና ምርጫችንን ማሳወቅ ብቻ አይደለም። ፍላጎቶቻችን ጫና ሲደረግባቸው እና ሲገፉ በዝምታ አለማለፍን ጭምር ያካትታል። መስመር ሲታለፍም በግልጽ ማሳወቅም አለበት። አስፈላጊ ሲሆን ጥሎ መሄድም ያስፈልጋል። ማናቸውም ቢሆኑ በመካከላችን ያለው ግንኙነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ እና የአቻዎች ግንኙነት መሆኑን ሊያውቁ ይገባል።
ፍላጎቶቻችን እና ምርጫዎቻችንን የምናሳውቀው “ሁሉም ሰው በእኔ ፍላጎት ዙሪያ ይሰብሰብ” ለማለት ግን አይደለም። “ሁሉም ሰው አገልጋዬ ይሁን” የሚልም ጥበቃ የለበትም። ነገሩ የሌሎችን ምርጫ መዘንጋት አይደለም፤ የሌሎችን እንደምናከብር ሁሉ የእኛም እንዲከበርልን መጠበቅ ነው።
እውነተኛነት
ግንኙነቶቻችን እንዲያበለጽጉ ከተፈለገ መሠረታቸው እውነተኛነት ሊሆን ይገባል። እውነተኛነት ከምንም በፊት የመተማመን መሠረት ነው። እውነተኛነት ከሚገለጽባቸው መንገዶች መካከል አንዱ እና ዋንኛው ከማስመሰል የጸዳ ሕይወት በመኖር ነው። እርስ በእርስ ያሉን ግንኙነቶቻችን በእውነት ላይ ሲመሠረቱ፣ በውስጣችን የምናስተናግደው ስሜት ሆነ ሀሳብ ከውጫዊው ቃላችን ሆነ አካላችን ጋር ስምረት ይኖረዋል፤ ሕይወታችን ተቃርኖም አያስተናግድም። ሀሳባችንን ለመግለጽም የምንይሉ ይሆን የሚለው ፍርሀት አይወረንም። ልዩነትን ማሳወቅም እንደ ችግር አይወሰድም፤ አንድ ዓይነትነትም እንደማይጠበቅብንም እንደማይጠቅመንም እንገነዘባለን።
ግንኙነቶቻችን መቼም ቢሆን ያልሆነውን እንድንተውን ሊጫኑን አይገባም። ሰዎች ልዩነታችንን መቀበል እና ማክበርም ይኖርባቸዋል። የተወደድነው እና ተቀባይነት ያገኘንበት ምክንያትም የተፈለግነው እኛን ስለሆንን ሳይሆን፣ እውነተኛን እኛን ስለሆንን መሆን አለበት። የተጨበጨበልን ቀን ከውስጣችን ጋር እየተጣላን ያሳለፍንበት ቀን ከሆነ በእርግጥም ግንኙነታችን መታከም ያለበት መሆኑን ያመላክታል።
እናም
በሚያበለጽጉ ግንኙነቶቻችን ውስጥ አንጣላም ማለት ግን አይደለም፤ ምናልባትም ከማያበለጽጉ ግንኙነቶች የበለጠ ሁሉ ልንጣላም እንችላለን። የመጣላቶቹ ዓይነቶች ግን ግልጽ ልዩነቶች አላቸው። ግንኙነቶቻችን ገንቢ ሲሆኑ፣ ግጭቶቻችን ጭምር የሚያፈረሱን ሳይሆኑ የሚገነቡን እና የምንማርባቸው ናቸው ማለታችን ነው። ግንኙነቶቻችን ግን በተደጋጋሚ ስለራሳችን ያለንን እንጥፍጣፊ በጎ አስተሳሰብ ቀስ በቀስ እየሸረሸሩ እና በራሳችን ያለን መተማመን እንዲቀንስ የሚያደርጉት ከሆነ ግን፣ በአቻነት መንፈስ የሚደረጉም አይደሉም፤ አንዳችም አይረቡንም።
የማያበለጽጉ ግንኙነቶች እንዲሁ መተው የለባቸውም። ማስተካከያ ካላደረግንባቸውም፣ ስሜታዊ ሕይወታችንን እና ለራስ ያለንን ግንዛቤ እጅጉን ይጎዱታል። በሂደት ተበድለን እንደ በዳይ መቆጠራችንን መቀበል እንጀምራለን፤ ለሌሎች እየራራን በራሳችን ላይ ግን ክፉኛ እንጨክናለን። እኛነታችንን በማይቀበሉ ሰዎች መከበባችንም ሰላማችንን ይነጥቀዋል፤ የራሳችንን ኑሮና ህልምም መኖር ያቅተናል። ኑሯችን በሂደትም ከሀቅ ያነሰ እና የማስመሰል ይሆናል። በማስመሰል መንገድ ደግሞ ማንም ለረጅም ጊዜ አይቀጥልም፤ ይሰለቻልም፤ በአምላክም ፊት ተቀባይነት ያለው መንገድም አይደለም። አንዳንድ የማይታረሙ ግንኙነቶችንም ጨክኖ ማቆም ይገባል። ግንኙነትን ማቆም ሁሉ መጣላት አለመሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል።
Written by : Dr. Tekalign Nega
Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.
Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.


Thank you. This is so helpful read.
Thank you, Dr. Tekalign for your message. If this message were shared on other social media platforms like TikTok, it could benefit many people.
Thank you. It was very interesting, insightful and very simple to understand. Blessings
Thank you so much. This is quite relevant.
I want to reflect that there’s always a struggle balancing between setting boundaries and the issue of reciprocity. Firm boundaries and reciprocating or a fair exchange of give and take.
A central problem I have observed these days is the issue of a sudden systematic, deliberate abandonment of some members in a team with out clear communication. Those who do the abandonment and the abandoned ones are both hurt and offended.
Additionally, the flourshing of subgroup dynamics which is the creation of ingroup vs outgroups seriously hurts friendships/teams
Thank you so much! It is a great message. It helped me to see my relationship with others. God bless you!