ጸሎታችን ቢመረመርስ?

በዶ/ር ተካልኝ ነጋ አንጎሬ

በጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ፣ በሃይማኖት የተገናኘንና ኋላ ላይ የቅርብ ወዳጅ ወደመሆን የደረስን አንድ ሰው ትዝ ይለኛል። ስሙን መጥቀስ አልፈልግም። ይህ ወዳጄ አሁንም ድረስ ያስገርመኛል። ከአምላክ ጋር ያለው ግንኙነት መልካም እንደሆነ ባሰበ ቀንና እንዳልሆነ ባሰበ ቀን ፍጹም የተለያየ ሰው ይሆናል።

ከአምላክ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳለው ሲያስብ፣ የኔን ሁኔታ እንኳ ለመጠየቅ አይሞክርም። እኔን እንደተሳሳተ፣ ራሱን ደግሞ እንደ ትክክለኛ አድርጎ ያስባል። በአንጻሩ ከአምላክ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳልነበረው ሲያስብ ግን እጅግ ትሁት ይሆናል።

ከአምላክ ጋር ያለው ግንኙነት ጥሩም ይሁን መጥፎ የሚለካው በጸለየበት ሰዓት ብዛት ነው። በጸለየ ቀን ስለ ራሱ ያለው ግንዛቤ አዎንታዊነት ይጎላበታል፣ ስለ እኔ ያለው አተያይ ደግሞ አሉታዊ ስለሚሆን እኔ ደግሞ ችግር ላይ እወድቃለሁ። የወቀሳ ናዳ ያወርድብኛል፣ በንቀት አይን እየተመለከተ ያልጠየቅኩትን ምክር ይዥጎደጉድልኛል። ከዚህም የተነሳ ባልጸለየ ቀን እረፍት አገኛለሁ። የእርሱ መጸለይ የእኔ መከራ መሆኑ አሁንም ድረስ ማስታረቅ የሚቸግረኝ ነው።

ይህንን በአስገራሚ ሁኔታ በተማሪነቴ ያየሁትን ነገር፣ መልኩን ቀይሮ በብዙ ቦታዎች ተመልክቼዋለሁ። “እንጸልያለን” በሚሉ አንዳንድ ሰዎች ላይ አስተውለዋለሁ። በጸሎታቸው ይኩራራሉ፤ በጸሎት ደካማ ነው ብለው የሚያስቡትንም ከመጤፍ አይቆጥሩትም። ጸሎታቸው መወዳደሪያና የደረጃ መለኪያ ሆኖ ትዕቢተኞች ያደረጋቸውም አሉ። በጸሎታቸው ይመጻደቃሉም ይመካሉም። ይህንን እውነት ማስተዋሌ፣ ስለ ጸሎት በአደባባይ በተደጋጋሚ የሚናገርን ሰው ሳገኝ ከመመቻቸት ይልቅ የመረበሽ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል።

ሰው እየጸለየ እንዴት ኩሩ ሊሆን ይችላል? ጸሎት ራሱ ትህትናና ራስን በአምላክ ፊት ማዋረድ አይደለምን? መጽሐፍስ ስለ ጸሎት ሲናገር ራስን ስለማዋረድ አይናገርምን (2ኛ ዜና 7፡14፣ ያዕቆብ 4፡10)? ከአምላክ ጋር በየቀኑ ለሰዓታት እንደምንነጋገርና እንደምንወዳጅ የምንናገር ሰዎች፣ ለጥቂት ደቂቃዎች እንኳ ከሰዎች ጋር በትህትና መነጋገር ለምን ይቸግረናል? በፊቱ ተንበርክከን የተገኘነው አምላክ፣ ጸሎታችንን ስንጨርስም አብሮን የለምን? ከአምላክ ጋር ያሳለፍነው ጊዜ ከአምላክ ባሕርይ የሆኑትን አያጋባብንምን? እነዚህ ጥያቄዎች በውስጤ ሲመላለሱ ዘመናት አልፈዋል።

ከጸሎት ጥያቄዎቼ ጋር ተያይዞ በሃይማኖታዊ ጉዞዬ አንድ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር፣ ጥቂት የማይባሉ አማኞች የአምላክን ቅናት የተረዱበት መንገድ ችግር እንዳለበት ነው። አምላክ የሆነ ምክንያት ፈልጎ ሊቆጣ ያሰበ አድርገን እንስለዋለን። አምላክ ከፍጥረቱ ጋር ያለው ግንኙነት ፉክክር የተሞላም ይመስለናል። ለአምላክ ያለን የተሳሳተ ግንዛቤና የሰጠነው የተሳሳተ ባሕርይ ጸሎታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።

የእግዚአብሔርን ቅናት የተሳሳተ መረዳታችን፣ አምላክ ከፍጥረቱ ጋር ያለውን ግንኙነት በትክክል እንዳንረዳ አድርጎናል። አምላክ ፍጥረትን በራሱ ፈቃድ እንጂ ተገዶ እንዳላስገኘው እንረሳለን። ፍጥረት የአምላክ የፍቅር ውጤት መሆኑንም አናስተውልም። አሁንም ድረስ በመግቦቱ እንደሚያስተዳድርና በእነርሱ በኩል ራሱን እየገለጸ ያለ አምላክ መሆኑን እንዘነጋለን።

ፍጥረትን የቸርነቱ ፈቃድ ውጤትና አሁንም በእርሱ መግቦት የሚተዳደር መሆኑን መዘንጋት ደግሞ፣ አምላክን ራሱ ካስገኘው ፍጥረት ጋር አላስፈላጊ ፉክክር ውስጥ የገባ ያስመስለዋል። አምላክ ግን ከፍጥረቱ ጋር የሚወዳደር አምላክ አይደለም። በፈጠረው ነገር በኩል ያገኘናቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ከአምላክ እንጂ ከሌላ አይደሉም።

አምላክንም “እኔ ብቻ” ባይ አድርገን ስለምንቆጥረው፣ በሕይወታችን ውስጥ የሌሎችን መኖር “ሌላ አምላክ” እንደማድረግ (የራስን ጣዖት መሥራት) ይመስለናል። ስለዚህም “ጣዖት አይሁንብህ” የሚለውን ማስጠንቀቂያ ያለምክንያት ከሁሉም ነገር በፊት እንደነቅረዋለን። ሥራውን፣ ልጆቹን፣ የትዳር አጋሩን ሆነ አንዳች ሌላ ነገርን የወደደ ችግር ውስጥ እንዳለ ይቆጠራል። ስለዚህም “ጣዖት እንዳይሆንብህ” በሚል ምክንያት የቅርብ ሰዎቻችን የሆኑትን የፍቅር ቃላትና እንክብካቤ እንዳያገኙ እናደርጋለን። አምላክ እኮ ለትዳር አጋራችንና ለልጆቻችን የምንገልጸው ፍቅር ልዩነቱ የሚጠፋ ማንነት አይደለም። በአምላክ ቅናት ስም ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆች እንዳያለቅሱ የከለከልንም ጥቂት አይደለንም። ጣዖትነት አምላክን ረስቶ ሌላ አምላክ መፍጠር መሆኑን እንረሳለን።

በአምላክ ላይ መደገፍ ከሌሎች ጋር ያለ መደጋገፍ ተቃራኒ አድርገን እንቆጥረዋለን። ስለዚህም ሌሎችን “ታስፈልጉኛላችሁ” ማለት የእምነት ማነስ ይመስለናል። አምላክ መጨቆንና መግዛት የሚፈልግ እንጂ የማይተባበር አድርገን ስለምንቆጥረው፣ “በእግዚአብሔርና በእናንተ ድጋፍ” ብለን ለመናገር እንቸገራለን። ከአምላክ እርዳታ ማግኘት ከሌሎች ያገኘነውን ተጨባጭ እርዳታ መካድ አድርገን የምናስብም ጥቂት አይደለንም። ስለ እናንተና በእናንተ በኩል ስለተቀበልኩት ነገር አመስጋኝ መሆን ብስለት እንጂ ችግር አለመሆኑን እንረሳለን። ስለዚህም መልካም ያደረጉልንን አምላክ እንዳስገደዳቸው አድርገን ማሰብን እንመርጣለን። ከልባችን የአክብሮት ምስጋናን ስላየነው ቸርነትና በጎነት ማቅረብ ይከብደናል።

አምላክም ከራሱ ሌላ ከሁሉም ጋር ጦርነት ውስጥ ያለ አድርገን ስለምንቆጥረው፣ ለአምላክ መወገንና ለሌሎች ደንታ ቢስ መሆን አንድ ዓይነት ይመስለናል። የአምላክ ጠላቶች ብለን እኛው የፈረጅናቸውን በአምላክ ስም ጠላቶቻቸው እንሆናለን። አምላክን መውደድ ሌሎችን መጥላት ይመስለናል። ከአምላክ ጋር መወገን ከሌሎች ሁሉ ጋር መቃረን ይመስለናልና ወደአምላክ የቀረብን ጊዜ ሁሉ ከሌሎች ጋር መጋጨት ያለብን ስለሚመስለን የመጣያ ምክንያት እንፈልጋለን፤ ከሌሎች እስካልተቃረን ድረስ ልክነት አይሰማንም።

ጤናማው የጸሎት አመለካከት ግን የተለየ ነው። ከምንም በፊት ሕይወታችን ከእርሱ የተቀበልነው ስጦታ መሆኑንና በአምላክ ላይ መደገፋችን ማሳያ ነው። መጸለይ አምላክን ሁልጊዜም እንደሚያስፈልገን መናገር ነው፤ በአምላክ ላይ ተስፋ ማድረግ ነው። ደካማነታችንንና እርዳታ ፈላጊነታችንን ማመን ነው። ከሁሉም በላይ ጸሎት ድካማችን የሚታገዝበት የመሠሪያ ቦታችን ነው። ተደጋፊነታችንን ስናውቅ ደግሞ ትዕቢት ጓደኛችን አይሆንም።

የጤናማ ጸሎት መገለጫው ርኅራኄ ነው። ጸሎት ጠንካራ ልባችንን ይሰብራል፤ ርኅሩኅ ያደርገናል። እንዴት? ጸሎት የአምላክን ኃይልና የኛን ድክመት በግልጽ ስለሚያሳየን ነው። ድክመቱን ያወቀማ አይኮራም። ይልቁንም ይራራል፤ ሌሎችን ለመውቀስ ያነሳውን ድንጋይ መልሶ ያስቀምጣል። ስንጸልይ ከምንም በፊት የምናውቀው ከሰዎች ተለይተን መልአክ መሆናችንን ሳይሆን ሰውነታችንን ነው፤ የካድናቸውን ድክመቶቻችንን ፊት ለፊት ስለምንጋፈጣቸው ለደካሞች የበለጠ እንራራለን። ይህም ከመቼውም በበለጠ በሌሎች ጫማ እንድንቆም፣ ስሜታቸውን እንድንጋራና በአጋዥነት መንፈስ አብረናቸው እንድንሆን ያስችለናል።

ጤናማ ጸሎት ለአምላክ ተናግሬዋለሁና ከእንግዲህ ወዲህ ምንም ኃላፊነት የለብኝም ማለት አይደለም። መጸለይ በጉዳዩ ላይ ማሰብንም ማቆም አይደለም። ሐሳባችንን አምላክ እንዲመረምረው፣ እንዲረዳው እና እንዲያግዘው ዕድል መስጠትም ነው። በአንድ ጉዳይ ላይ ደጋግሞ መጸለይም ለነገሩ በልባችን ውስጥ ቦታ መስጠት መሆኑንንም እናስተውል። በልባችን ውስጥ የቆየ ነገር ደግሞ እናስባለን። የምንጸልየውም እጆቻችንን ለማጣመር ሳይሆን ያለብንን እርምጃ ለመገንዘብና የሚያስፈልገንን ጸጋ ከአምላክ ለመቀበል ይሆናል። መጸለይ የኛን አድራጊነትና ፈጻሚነት ትተን ወደ ተናጋሪነትና ቸልተኝነት የሚቀይረን ግን አይደለም።

እውነተኛው ጸሎት በሕይወታችን የምናያቸውን መልካም ነገሮች ሁሉ መወዳደሪያ እንድናደርጋቸው አይፈቅድልንም። ያለን ነገር ሁሉ ከአምላክ የተቀበልነው መሆኑንም እንድናስተውል ይረዳናል። ያለን ሁሉ ከቸርነቱ የተቀበልነው እንደሆነ በመረዳትም ከመቼውም በበለጠ አመስጋኞች እንድንሆን እውነተኛ ጸሎት ያግዘናል። የአምላክ የፍቅር መገለጫ አድርገንም ያሉንን በጎ ነገሮችን እንቀበላቸዋለን እንጂ ከሌላው ጋር መወዳደሪያ አናደርጋቸውም። ያኔም ምስጋና በውስጣችን የሚፈልቅ ቅኔ እንጂ አምጠን የምንደረድራቸው ቃላት አይሆንም።

ከመጸለያችን በፊት ሆነ በኋላ ራሳችንን መፈተሽ አንርሳ። ያኔም ጸሎት መቼም ቢሆን መኩሪያችን እና መታበያችን እንዲሆን አንፍቀድለትም። የጸለይን ቀን ሰማያትን ደግፈን የያዝን ያልጸለይን ግን ሰማያት የመውደቅ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ከማሰብ እንቆጠባለን። በሥልጣኑ ቃል ሁሉን የሚደግፍ እግዚአብሔር እንጂ እኛ እኛ አለመሆናችንንም ማስተዋል ይሆንልናል።  ከሁሉ በፊት  ከአምላክ ጋር እያሳለፍን ነው የምንለው የጸሎት ጊዜ በእርግጥም የተሻለ ሰው እያደረገን እንደሆነ እንጠይቅ።

አጸላያችንንም እንመርምር። ጸሎታችን ከትህትና ጋር መቼም እንዲፋታ አንፍቀድ። ጸሎታችን በአምላክ ላይ ያለ ተደጋፊነታችንን፣ የእርስ በእርስ ተደጋጋፊነታችንን እና  ደካማነታችንን ሁልጊዜ ማስታወሱን እናረጋግጥ። በሌሎች ቦታ ሆነን ነገሮችን የምናይበትን ልብ ያስፋልን እንጂ ጸሎታችን ዕይታችንን አያጥበው። ጸሎታችን ግድየለሾችና ተግባራዊ እርምጃ የማንወስድ ሰዎች እንዳያደርገንም እንጠንቀቅ። መጸለይ የማሰብ ተቃራኒ አለመሆኑንም እናስታውስ፤ የምንጸልየው ላለማሰብ ሳይሆን በትክክል ለማስብ መሆኑንን አንዘንጋ።

ከሁሉም በላይ ቅዱስ ጸሎታችንን ሌላ የመኅበራዊ ሕይወታችን የመወዳደሪያ መሣሪያ አናድርገው። በጸሎታችን እንደግ እንጂ በጸሎት ውስጥ የምናያቸው ክፍተቶች መጸለይን የየዕለት ልምምዳችን ከማድረግ አይጎትቱን። መቼም ቢሆን ወደማንጸልይበት ደረጃ እንዳንደርስ እንጠንቀቅ፤ ትህትናም ልብሳችን ይሁን።

Share This Story, Choose Your Platform!

Written by : Dr. Tekalign Nega

Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.

Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.

Subscribe To My Page

BE NOTIFIED ABOUT RECENT UPDATES

One Comment

  1. Betel May 21, 2025 at 5:11 am - Reply

    It is a great message, prayer is communicating with God that we talk to Him and listen His voice. May we grow to have fruitful prayer life and close relationship with Him. May God bless you more!

Leave A Comment