ሃይማኖት እና ሀገር

በ ዶ/ር ተካልኝ ነጋ አንጎሬ (PhD)

ሃይማኖት እና ሀገር በጣምራ ሲነሱ ጎልቶ የምንሰማው ድምጽ “ሐይማኖት የግል ነው፤ ሀገር ግን የጋራ ነው።” የሚለውን ነው። ብሂሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የቀመሩት ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ እንደሆኑ ይነገራል። ንግግሩን በሁለት በኩል እንደተሳለ ቢላዋ ልናየው እንችላለን፤ ፈቃጅም ከልካይም ነው። በአንድ በኩል የሐይማኖትን ነጻነትን ለግለሰቦች የተወ ይመስላል፤ በሌላ በኩል ስናየው ደግሞ የሐይማኖትን ሚና ከማኅበራዊ ጉዳዮች የሚያገል ይመስላል።

ብዝሀነት ባለበት አገር ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ ሐይማኖትን እንደ ግላዊ ጉዳይ መታሰብ አለበት የሚለው እምነት የሚጋሩ እንደ ፈቃጅ ያዩታል። እኚህ አባባሉን ነጻነት ሰጪ፣ ጥበብ እና እንደ የመቻቻል መንገድ አድርገው ቢመለከቱት በእርግጥም አይፈረድባቸውም።

ሐይማኖታዊ ማንነትንም ሆነ ተያያዥ እሴቶቹን በቀላሉ እንደ ኮፍያ የምናወልቀው እና የምንደርበው አድርገን ለማናይሳ? የአባባሉ ከልካይነት ይጎላብናል። አምላካችን የማይገዛው የማንነታችን አካል ወይም ፍጥረት የለም ብለን የምናምን አምላክን የምናገልበት ቦታ እንዲኖረን አንሻም። ስለዚህም በብሂሉ የምንሰማው ሐይማኖት የእኛ ወይም የጋራ የምንለው ቦታ ድርሽ ባይል ይሻላል የሚለውን አንድምታ አንወደውም። መፈክሩ ሐይማኖቱ የጋራ ነው ብለን የምናስባቸው ማኅበራዊ ምህዳሮቻችን ላይ ባይመጣ ይሻላል የሚል ምኞትንም አንጋራም።

ታሪካዊ ፍርሃት

ሐይማኖታችን የጋራ ምህዳራችን ውስጥ እንዳይመጣ ለምን ሰጋን? ወደን አይደለም። ነገሩ ከሐይማኖት ብዝሀነታችን እና ብዝሀነታችንን በታሪካችን ውስጥ ካስኬድነበት መንገድ ጋር ይያያዛል። አገራችን ውስጥ ሁሉም ሐይማኖቶች እንደ እኩል እና አቻ ለዘመናት አልታዩም። አንዱ እንደ ልጅ ሌላው እንደ እንጀራ ልጅ የተቆጠሩባቸው ዘመናት በአብሮነታችን ውስጥ ረጅሙን ዕድሜ ይወስዳሉ። ከመንግሥት ጋር የተጠጋጉ ሐይማኖቶች ነበሩን። እኚህ ሯሳቸውን ሲጠቅሙ ሌሎቹን አግልለዋል፤ አንዳንዴም አጥቅተዋል። እነዚህን ጊዜያትስ ማን ይናፍቃል?

ሕግ ሁላችሁም እኩል ናችሁ ካለን ወዲህስ? መሻሻሎች አሉ፤ መሰማቱ ሌላ ሆኖ ሳለ ቢያንስ ሁላችንም ስለመብታችን መከራከር የምንችልበትን ድፍረት አጎናጽፎናል፤ የምናጣቅሳቸውም የሕግ አንቀጾችም አሉን። አንዳችን ሌላችንን እንደ አቻ የመቁጠር ልባችንስ? ከሕጉ መንፈስ እጅጉን ይርቃልና መጠቃቃታችን ቀጥሏል። ሐይማኖቶቻችን መካከል ከይስሙላ ያለፈ ልባዊ መቀባበል እምብዛም አይታይም፤ ግንኙነታችንም የጦርነት ይመስላል፤ አንዳችን ሌላችንን የሐይማኖታዊ ማንነታችን ስጋት አድርገን ማየታችንም ከሞላ ጎደል ቀጥሏል። የይስሙላውን የአደባባዩን መከባበር ከጓዳው መናናቅ ጋር የተመለከቱትም በማኅበራዊ ምህዳር ላይ ሐይማኖት መምጣቱ ሌላ ብጥብጥ ቢያመጣ እንጂ ይሄ ነው የሚባል አዎንታዊ ሚና የለውም የሚል አመለካከት ቢያዳብሩ ይፈረድባቸዋልን?

አዲሱ ለውጥ

ወደድንም ጠላንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነገሮች መለወጥ ጀምረዋል። “ሐይማኖት የግል ነው” የሚለው መፈክር እየተሸነፈ ነው። ፖለቲካን እንደ ኮረንቲ በሩቁ ሲሉ የነበሩ የሐይማኖት መሪዎች ጭምር አመለካከታቸውን ዳግም መቃኘት እና ማኅበረ ምእመናኖቻቸውን መቆስቆስ ጀምረዋል። የአገራችን መልክ በሌሎች ተዋጠ እና አደባባዩ በእኛ መወረስ አለበት የሚሉ ሐይማኖተኞች ከመቼውም በበለጠ በዝተዋል። የሐይማኖት መሪዎች ምእመናኖቻቸውን በፖለቲካው መስክ ተሳትፈው የእኛ ናቸው የሚሏቸውን ፍላጎቶቻቸውን እንዲያስፈጽሙላቸው መጎትጎት ጀምረዋል።

ከውስጣዊው ጉትጎታ የተነሳም የጋራ ማኅበረሰባዊ ምህዳሮቻችን ላይ ከዚህ በፊት በሐይማኖታዊ አጥባቂነታቸው ብቻ የምናውቃቸው ግለሰቦች በፖለቲካው ሆነ በሌሎች ማኅበራዊ መስኮችም ብቅ ማለት ጀምረዋል። የእምነት ቤተሰቦቻቸው ውስጥ ተቀባይነት ያላቸውን ሰዎችም በተለያዩ ደረጃዎች በማኅበረሰብ ውስጥ ተሳትፎ ሲያደርጉም እያየን ነው። መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ሐይማኖቶች የእኛ እንቁዎች ናቸው የምንላቸውን የእምነት ቤተሰቦቻችንን የጋራ ማኅበራዊ መስኮቻችን ላይ አሰማርተናል።

ሐይማኖታዊ ድምጾቹ

ከሐይማኖት መንደራችን ወደ አደባባዮቻችን የላክናቸውን ምዕመናንን ግን ምን ዓይነት ናቸው? መገኘታቸውስ ምን ዓይነት በጎ ለውጥ አመጣ? ይኽንን ለመመለስ በማኅበራዊ መስክ ላይ ብቅ ብቅ ያሉትን ሐይማኖተኞች ድምጽ በአንክሮ ማድመጥ ያስፈልጋል።

የሐይማኖታቸው ጉዳይ ከንክኗቸው ወደ ጋራ አደባባዮቻችን የመጡ ኃይማኖተኞች ልበ ሰፊ አይደሉም የሚያስብሏቸውን ሦስት መገለጫዎች እናንሳ። አንደኛው መለያቸው ቡድንተኝነት ነው። ሁላችን ያለንበት አደባባይ ሐይማኖቶቹ ወጡ እንጂ ከቀደመው ሐይማኖት ቅጥሮቻቸው አልወጡም። የዚህ ማስረጃውም በጋራ አደባባይ ላይ የሚናገሩዋቸው ንግግሮች ሆኑ ተግባሮች ሌላው መኖሩን እውቅና የማይሰጡ መሆናቸው ነው። ለሐይማኖታቸው ማድላትም ይታይባቸዋል። ጥብቅናቸው እምነታቸው ለቆመለት ሐቅ እና እውነት ሳይኾን ይገባናል ለሚሉት ለራሳቸው ጥቅም ነው። እኚህ ቢሳካላቸው አገራችን የእነርሱን ሐይማኖት እንድትመስል የሚሹ ናቸው።

ማኅበራዊ መስክ ላይ ብቅ ያሉት ሐይማኖተኞች ሁለተኛው መለያቸው የዕይታ ውስንነት ነው። ሕይወት ሐይማኖት ከሚባለው ፍላጎት ባሻገር ሌሎች ደርዞች እንዳሉትም የሚገነዘቡ አይመስሉም። ጥቃቅን በሚባሉ ሐይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ እንዳላየናቸው ሁሉ በሌሎች ማኅበረዊ ጉዳዮች ላይ ግን ድምጻቸው ሲሰማ አይደመጥም። የከበበን ጉስቁልና፣ ጭቆና፣ የነጻነት መታጣት፣ የተንሰራፋው ሌብነት፣ ተስፋ የማጣቱ ጥግ፣ ትርጉም አልባነቱ፣ እና መሰል ጉዳዮች ሁሉ የቤት ሥራዎቻችን መሆናቸውን ሐይማኖተኞቹ ገና የተገነዘቡት አይመስሉም።

ማኅበራዊ መስክ ላይ የምናያቸው ሐይማኖተኞች ሦስተኛው ውስንነታቸው የሐይማኖታቸውን መልዕክት ከተከታዮቻቸው ባለፈ ለሌሎች ማስረዳት እና ማስረጽ አለመቻላቸው ነው። የለመዱት መስበክ እንጂ መወያየት አይደለም። ፍላጎታቸው እንዲደመጡ ብቻ እንጂ ማድመጥ የለበትም። ከተግባሮቹ ባሻገር ያለውን ዕሴት እና መልእክት መረዳትም ሆነ ማስረዳትም ይቸግራቸዋል። ቋንቋውም ሆነ ክህሎቱም የላቸውም። ከመካከላቸው ቋንቋውንም ሆነ ክህሎቱን ያዳበረውን የእምነት ማኅበረሰባቸው በጥርጥር እንዲያያቸው ዘመቻም ይከፍቱባቸዋል።

እነዚህ ሦስት መገለጫዎች ምን ያሳዩናል? የእኛን የሐይማኖት ሰዎች ወደ ጋራ ማኅበራዊ ምህዳሮቻችን ውስጥ የላክናቸው በብልጠት እንጂ በተልዕኮ ስሜት አለመሆኑን ይጠቁሙናል። የላክናቸው የአምላክ መንገድ ምድራዊ ምስክሮች ሁኑ ብለን ሳይሆን የሥልጣን አምላኪዎች ስለሆንን ነው። ያሰማራናቸው የሐይማኖት መሪዎቹ ሆንን ተሰማሪዎቹ ራሳችንን በጋራ ማኅበራዊ ምህዳር ላይ ያገኘነው ከስልጣኖቹ መጉደል የሚያሳጣን ነገር አለ በሚል ቅኝት ነው። ዕቅዳችንም ፊት ለፊት ማግኘት ያቃቱን ነገር ግን ይገባናል ብለን የምናምናቸውን ጥቅሞቻችንን በኋላ በር በኩል ይመስሉናል ብለን በምናምናቸው ፖለቲከኞች አማካኝነት በአቋራጭ ማስፈጸም ነው። እናሳ? ሐይማኖተኞቹ ፋይዳ ያለው ሚናን በማኅበረሰባዊ ምህዳራችን ውስጥ እንድንጫወት ከተፈለገስ? ሥር ነቀላዊ ለውጥ እኛ ጋር ይፈለጋል። ከሁሉ በፊት በአምላክ ስም ከአምላክ ያነሰ ልብ ይዘን አደባባይ መውጣታችንን ማቆም አለብን። ሁሌ የምናቀነቅነውም የእኛን ጉዳይ ብቻ መሆኑም ማብቃት አለበት። የእኛ የምንለው ጉዳይ የከነከነን ያክል የሌሎች ጉዳይ ዕረፍት ሊሰጠን አይገባም። የአምላክ እንደራሴነት የእኛን ፍላጎት የአምላክ አድርጎ ማቅረብ እንዳልሆነም ስለምንረዳም ፍላጎቶቻችንን በአምላክ ፊት አቅርበን ራሳችንን የምንመረምርበት የውስጥ ዓይንም ያስፈልገናል።

ከላይ የጠቀስናቸውን መሻሻሎች ሳናደርግ ተሳትፏችንን ብናጧጥፍስ? ከአምላክ ባነሰ ልብ በአምላክ ስም እንደ አምላክ እንደራሴ በድፍረት በመናገራችን እንወክልሃለን የምንለውን አምላክ ራሱ እንደ እኛ ጎጠኛ እናስፈርጀው እና እናሰድበዋለን። ብዙ ማስተካከያ የሚያስፈልገውን ማኅበራዊ ምህዳሩን መገኘታችን ግን አያስውበውም። የእኛን የሚለውን ጠባብ የቡድንተኝነት ቅኝት በሁሉን አካታቹ የሁላችን ዕይታ ሳንተካ በሐይማኖት ስም ዘለን ማኅበራዊ ምህዳር ውስጥ መግባታችን ሌላ ተጨማሪ ብጥብጥ ቢያመጣ እንጂ ሰላም አያወርድም።

በንግግሮቻችን ውስጥም ከሐይማኖታችን ጉዳይ ውጭ ያሉ ጉዳዮችን ችላ በማለት ከቀጠልንስ? አምላካችንን ከራሱ ውጭ ለፍጥረቱ ግድ የሌለው ተደርጎ እንዲሳል መንገድ እንከፍታለን። በንግግራችን እና በድርጊታችንም አምላክ ከእኛ ሰዎች ጋር ያለው ሙግት ከእውነት እና ከፍትሕ ጋር የተቆራኘ መሆኑን እንዲዘነጋም መንገድ እንከፍታለን። የእምነት ማኅበረሰቦች የምናሰማው ድምጽ አምላክ አሁንም ድረስ ደጋግፎ ፍጥረቱን የሚያስቀጥል፣ የሚያወጣ እና የሚያስገባ፣ በቸርነቱም እየመራ ያለ መሆኑ ሊያሰምርበት ይገባል። መልዕክታችንን ያየ የአምላክን ለፍጥረቱ ያለው ፍቅር፣ ለእውነት የሚሰጠውን ዋጋ፣ እና ለፍትሕ ያለውን ተሟጋችነት ካላስረዳ ምስክርነታችን ካደው እንጂ አላሳየውም።

ሐይማኖተኞቹ አስተዋጽኦዎቻችን ከሐይማኖታችን አስተምህሮ ውስጥ ቢቀዳም ከእኛ ዘሎ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ስሜት መቃኘት አለበት። በሐይማኖታችን የተቃኘው ማኅበራዊ አስተዋጽኦ እንዲጠቅም ከተፈለገ ትኩረቱ ለራስ መብት በመታገል ብቻ መወሰን የለበትም። ትግላችን የምንለው ማንኛውም ነገር ሁላችንም ታሳቢ ሊያደርግ ይገባል። አሊያማ ማኅበራዊ ምህዳሩ በእኛ ይገዛ ወይም እኛን በተለየ መንገድ ያገልግል የሚል ጠባብነት ይሆናል፤ ትግላችንም ሐይማኖታዊ አገርተኝነት እንጂ ሌላም አይሆንም።

ሐይማኖታዊ አስተዋጽኦ እንዲሰፋ ከፈለግን ድምጽ የምናሰማው የእኛ ማኅበረሰብ አጥር ሲነቀነቅ፣ የሐይማኖት መሪዎቻችን ሲሰደቡ ብቻ መሆን የለበትም። የድሆች እና የግፉአንን ድምጽ ችላ ብለን በአምላክ ሥም እንናገራለን ብንል ትርጉም እንደሌለው መገንዘብ ይኖርብናል። የማኅበረሰባችን የሞራል ዕሴቶች መሸርሸር ሳይቆጠቁጠን ትንሽ በተነካን ቁጥር ያለ ልክ ብንጮኽ እንኳን አምላክ ሰውም ደስ አይሰኝብንም። የጋራ የሚባለው ምህዳር ውስጥ ተመጥኖ የጋራ ጉዳዮችን አጀንዳ ማድረግ አለመቻል ያሳስባልም ያሳዝናልም።

ሐይማኖተኞቹ እንደ ማኅበረሰብ በጋራ እየገጠሙን ባሉ ጉዳዮች ላይ መወያየት እና አማራጭ ሀሳቦችን ማቅረብ አልቻልንበትም። አቀራረባችንም ሌላውን ወደ እኛ ለመለወጥ የሚደረግ ትግል እንጂ ውይይትም አይመስልም። አሁንም ድረስ ከቡድናችን የሚያልፍ ማኅበራዊ አንድነትን በምንግባባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ መፍጠር አልቻልንም። ስለዚህም ከራሳችን የእምነት ማኅበረሰብ ባለፉ ሐይማኖታዊ ጉዳዮችን ስንጠይቅ ሆነ የጋራ ብለን በምናምናቸው እንደ ፍትህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ስንሳተፍ አልታየንም።

ግን ለምን?

አብዛኞቹ ችግሮቻችን የሚመነጩት ስለ አምላክ፣ ስለ ራሳችን እና ስለተልእኮዋችን ካለን የተዛባ ግንዛቤ ነው። አምላክ የእኛ ብቻ ይመስለናል። ስለዚህም እኛ በጮኽን ቁጥር አብሮን የሚጮኽ እና ደስ በተሰኘን ቁጥር ጮቤ የሚረግጥ አስመስለነዋል። አምላካችን ግን ከእኛ ስሜት ስሜቱ እና ፍላጎቱ ይልቃል፤ ሁላችንንም የሚሰማ እና ስለሁላችን ግድ የሚለው ማንነት ነው። ተልእኮዋችንም ያየነውን የአማልክን አፍቃሪያዊ፣ ፍትሀዊ እና የምህረት እና የርህራሄ አተያይ ለሌሎች ማሳየት ነው።

ሁለተኛው ችግራችን ፍርሃት ነው። እኛ ሐይማኖተኞቹ ላይ የወደቀው ፍርሃት ሀገሩ ሁሉ ላይ የወደቀው ፍርሃት ተጋብቶብናል። የጋራ ብለን በምናስባቸው ጉዳዮች ላይ መናገር የፈራነው በሌሎች ላይ ያደረሰውን በእኛ ላይ እንዳይደርስም ከመስጋት ነው። ስለዚህም በአካታችንነት እና በብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከተናገርን አሁን ላይ አለን የምንለውን “የአምልኮ ነጻነት” ከናካቴው እንዳናጣው ወይም ምቾታችን እንዲነካብን አንፈልግም።

ሁላችንም የምንፈልገው የነቢይነቱን ክብር እንጂ ነቢያዊ ተልእኮ የሚያስከትለውን ስደት አይደለም። ስለዚህም በአምላክ ስም አደባባይ ወጣን እንጂ የአምላክ ድምፆች የመሆኑን በረከት አልታደልንም። በዚህ ቅኝታችን ያጎደልነው መሆን ያለበትን ብቻ አይደለም፤ መሆን የሌለበት ነገር እንዲሆን መጠቀሚያዎች ጭምር ሆነናል። በዝምታችንም ሆነ በንግግራችን ተንሰራፍቶ ያለውን ኢፍትሀዊነት አጽድቀናል። አምላክ የሚሰጠውን ተስፋ ለሕዝባችን እንዳንመግብ ከልክሎናል። በኢፍትሀዊነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን እና ተቃውሞዎችንም በአዎንታዊነት አንዴ ሳንደግፍ ተቃውሞዎችን ሁሉ ለመኮነን ግን ከማንም በፊት አደባባይ ተሰልፈናል።

እናሳ?

ሐይማኖተኞቹ ተሳትፏችን ፋይዳ እንዲኖረው ከፈለግንስ? ከምንም በፊት የአምላክን ልብ እንወቅ። አምላካችን የሁሉ አምላክ እና ስለ ሁሉ ግድ የሚለው መሆኑን ላፍታም አንዘንጋ። ለእውነት፣ ለፍትህ፣ እና ለግፉአን ያለውን ልብም ሁሌ እናስታውስ። እጅግ እንለያቸዋለን ከምንላቸው ሁሉ ጋር የምንጋራው የጋራ ሕይወት እንዳለንም እንዘንጋ። ሌላውን የምንቀርበው ልንነግረው ብቻ ሳይሆን ልናዳምጠውም ይሁን። በእርግጥም የአምላክ እንደራሴዎች ከሆንም አምላክ ልብ ልክም ልባችንን ለማስፋት ፈቃደኝነት ይኑረን።

Share This Story, Choose Your Platform!

Written by : Dr. Tekalign Nega

Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.

Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.

Subscribe To My Page

BE NOTIFIED ABOUT RECENT UPDATES

Leave A Comment