ንዴት

በ ዶ/ር ተካልኝ ነጋ አንጎሬ (PhD)

መልኩ እና መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁላችንም እንናደዳለን። የአንዳንዳችን ቁጣ የሚንበለበል እሳት ነው፤ የሌሎቻችን ልዝብ ሊባል ይችላል። የተወሰነው አንዴ ከተቆጣን በቶሎ መብረድ ሲከብደን ሌሎቻችን ምልስ ነን። የቀረነው ሁሌ ቱግ ብለን ስለምንገኝ ንዴት መታወቂያችን ሆኗልና የምንፈልገውን ትኩረትም አያስገኝልንም።

መልካሙ ዜና ቁጣችንን የጋራ ገንዘባችን ማድረግ የምንችለው ነገር መሆኑ ነው። ንዴታችን መጠን አልፎ ለሥነ ልቦናዊ ውጥረት እንዳይዳርገን፣ ዋጋ የምንሰጣቸውን ግንኙነቶቻችንን የበለጠ እንዳይጎዳቸው እና ነገሩ ወደ አካላዊ እና ስሜታዊ ጥቃት እንዳይሸጋገር ማድረግ በእርግጥም ይቻላል።

በዚህ መጣጥፍ ውስጥ ትኩረታችንን አንዳችን በሌላችን ላይ የምንገልጻቸው ንዴቶቻችን ላይ እናድርጋለን። ንዴታችንን እንዴት እንግለጽ የሚለውም ዋንኛ ጉዳያችን ነው። ግባችንም ንዴታችን ሌላ ጥል ለመፍጠር ተጨማሪ ቤንዚን ከመሆን ይልቅ እርቅ እና ሰላምን እንዲያሰፍን ሚናን እንደምንጫወት ግንዛቤ መስጠት

ስንቴ?

በጥቅሉ እናውራ ካልን ግን ሳንናደድ ያለፍናቸው ቀናት ካሉም በቁጥር ጥቂቶች ናቸው። ተማሪዎችን እንደ ናሙና በመውሰድ የተደረጉ ጥናቶች ላይ ጥናቶችም በአማካይ በሳምንት 7ቴ እንደምንናደድ ያሳያሉ፤ በአማካይ በቀን አንዴ እንደማለት ነው። እርግጥ ነው ይኽ ቁጥር ዕድሜያችን 30 ሲደፍን በሳምንት ከ3 እስከ 5 ጊዜ ይሆናል።40 ሲሞላን ደግሞ በሳምንት 1ዴ እና 2ቴ ወደመሆን ይወርዳል። የሚወርደው ታዲያ የምንናደድበት መጠን ብቻ ሳይሆን የንዴታችን መጠን ጭምር ነው። ከ30ዎቹ በፊት ንዴታችን ተንቀልቃይ የሚባለው ዓይነት ነው፤ ክሚያለማው የሚያጠፋው ይበልጣል።ከ30 እስከ 50 ደግሞ መጠነኛነት ይታይበታል፣ 50ዎቹ ሲሞላን ንዴታችን ትንሽ ይሆናል። ጡረታ የመውጫችን 60 ዓመት ሲደርስ ንዴታች ተከፋ ወይም ተረበሸ ብቻ የሚባል ሰው የምሆናችን ዕድል እጅግ ከፍተኛ ነው[1]

አብዛኞቹ ንዴቶች ምንጫቸው የእርስ በእርስ ግላዊ ግንኙነታችን ናቸው። እርግጥ ነው እኛ ሰዎች ወፏ ለምን ኩሷን ጣለችብኝ እና አየሩ ብራ ከመሆን ይልቅ ለምን ጨላለመ ሁሉ ብለን መቆጣት የሚችል ማንነት አለን። ከሰዎች ይልቅ በነገሮች ላይ የምንናደደው ግን ከስንት አንዴ ነው። ከተናደድንባቸው 100 ጊዜያት መካከል 88ቱ የሚመነጩት ከግለሰባዊ ትሥሥሮቻችን ነው፤ በአብዛኛው የምንናደደው ከሰዎች የተነሳ ነው። የሚሰነዘሩትም ከማንግባባው ሰው ይልቅ በምንወደው (33 ከመቶ) እና ቅርርብ ባለን (21 ከመቶ) ሠው ላይ ነው።[2] ግድ በሌለን ሰው ላይ የመቆጣት ዕድላችን በእርግጥም አነስተኛ ነው። ለምን ማድረግ የሌለብኝን ነገር አደረኩ በሚልም በራሳችን ላይ የምንቆጣባቸው ጊዜያትም እንዲሁ አሉን። ራሳችን መቆጣታችንንም መልሰን እንዳንደግመው ማስተማርም ይመስለናል።

አንዳንዴ የምንቆጣው በአምላክ ላይ ይሆናል። በሕይወት መንገዳችን ለምናልፍባቸው መከራዎች አምላክ ተጠያቂ እናደርጋለን። ልባችን ከእርሱ ጋር እያለ እና  በመንገዱ እየሄድን ብቻችንን እንደተወን እንዲሰማን የሚያደርጉ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ያኔም እንደ መዝሙረኛው ዳዊት እንደሚታረዱ በጎች አደረከን፣ በተንከን፣ በዋጋ ሸጥከን፣ መሳለቂያ አደረከን ብለን አምርረን እንናገራለን።[3]  ጥሩነቱ አምላክ እንዲህ ዐይነት መዋቀሱን በደፈርከኝ ስሜት አለማዳመጡ ነው። ከነንዴታችን አምላካችን ጋር መምጣታችን አሁንም ድረስ ልባችን ውስጥ ቦታ እንዳለው እና ከእርሱ ሌላ መሸሻ እንደሌለን የሚያመላክት ስለሆነም እንዳለማመን ሳይሆን እንደ እምነት ንግግር ይወሰድልናል። መልዕክታችንም ታዳጊው አንተህ ነህ እባክህ ተነስ ታደገን ነው፤ የተናደድንበት አምላክ ራሱም ሚስጥራዊ ሊባል በሚችል መገኘቱም ያረጋጋናል።

ስለ ንዴት ስንነጋገር ከሁሉ በፊት ማስመር የሚገባን ነገር ንዴት ሁሉ መጥፎ  ነው የሚለውን ግንዛቤ ስሕተት መሆኑን ነው። እንደውም መቼም አለመናደድም የጤና ምልክት አይደለም። ፍትህ ሲዛባ እና ሰው ሲጠቃ አለመናደድ የሥነ ልቦና ችግር ምልክትም ነው። ንዴታችንን በተገቢው ሁኔታ መግለጽ አለመቻልም ለበርካታ ችግሮች ያጋልጠናል። እንዳይገለጥ ደጋግመን የተጫነው ንዴት ለደም ግፊት ሊያጋልጠን ይችላል። ከመጠን ባለፈ መልኩ እንድንበላ፣ እንድንጠጣ፣ ሲጋራ እንድናጨስ እና አደንዛዥ እጽ እንድንወሰድም ይገፋፋናል። የልብ ችግር፣ ድባቴ፣ ደም ግፊትም የመያዝ ዕድላችንም ከፍተኛ ነው። ንዴታችንን በትክክል መያዝ ደግሞ የደም ግፊታችን እንዳይጨምር እና የተሻለ ጤና እንዲኖረን ያግዘናል። [4]

የሚሻለው መንገድ

ለንዴታን የሚገጥመን ምላሽ ተጨማሪ ንዴት ወይም እኛን መረዳት ሊሆን ይችላል። ንዴታችን የሚሰጠው ምላሽ ሌላ ንዴት የሚሆነው መቼ ነው? በአብዛኛው ንዴታችንን የገለጽንበት መንገድ የተናደድንበትን ሰውን ጥፋተኛ አድርጎ የሚከስ እና ፈራጅ ሲሆን ነው። መቼም ንዴታችን ንቀትን እያንጸባረቀ ብሎም በጥፋተኝነት ሌላውን እየከሰሰ ከከሰስነው ሰው በጎ ምላሽ መጠበቅ ሞኝነት ይሆናል። ንዴታችን ሌላ ንዴትን የወለደበት ምክንያት ግልጽ ነው። እየተከሰሰ ያለው አድማጫችን ንዴታችን ሊጎዳን ያሰበ የቃላት ጡጫ አድርጎ ስለሚረዳው ነው። በንግግራችን እየተጠቃ እንደሆነ ከሚሰማው ሰውስ ምን እንጠብቃለን? ምላሹ ከመረዳት ይልቅ ወደ መከላከል ያዘነብላል።

የእኛው ንዴት ሌላ ንዴትን እንዳይወልድ ማድረግ ይቻላልን? ንዴታችን ከሌላ ጥል ይልቅ አንዳችን ሌላችንን እንድንረዳ ደግሞም እንድንታረቅ መንገድ ሊከፍትልን ይችላልን? መልሱ አዎን ነው። ንዴታችን መልካም ነገር ይዞ እንዲመጣ ካሰብን ንዴታችንን የምንገልጽበት መንገድ ከተለመደው እጅጉን መለወጥ አለበት።

የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ንዴታችን የምንፈልገውን ትኩረት እና ለውጥ እንዲያስገኝ ትኩረቱ ካናደደን ሰው ይልቅ ወደተናደድነው ወደ እኛ ማተኮር እንዳለበት ያስረዳሉ። ትኩረታችንን ከአናደደን ሰው ተነስቶ ወደ እኛ ዞረ የሚባለው ንዴታችንን ራሱን መአከል አድርጎ መግለጽ የሚችልበትን መንገድ ስናመቻችለት ነው። ንዴታችን የተገለጽበት መንገድ መአከሉ እኛው ከሆንን ሌላውን ሰው የማስቆጣት ዕድላችን ያንሳል። የዚኽ ምክንያትም ንዴታችን እያደመጠ ያለው ሰው ራሱን እንደተጠቂ እንዳይመለከት ስለሚያግዘ ነው። የሄኔ ትኩረችንም የተሰማንን ስሜት በመግለጽ እና የተፈጸመው ተግባር ለእኛ የሰጠንን ትርጉም በማሳወቅ እና ጥበቃችንን በማሳየት ላይ ያተኩራል።

ትኩረታችን በእኛ ላይ የማድረጋችን ፋይዳው ምንድን ነው? ከምንም በፊት ለንዴታችን ኃላፊነትን እድንወስድ ያደርገናል። መልእክቱ የተናደድነው እኛ ነን ባይ ነው፤ የተናደድንበት ምክንያትም የሆነውን ነገር ከተረዳንበት ምክንያት ጋር ይያያዛል። ይኽ ዐይነቱ አገላለጽ እና የንዴት መረዳት ንዴት ከቁጥጥራችን ውጭ ያለ ነገር እንዳይሆን በማስገንዘብም በቁጥጥራችን ሥር እንዲሆን ይረዳዋል።

ሁለት የተለያዩ የንዴት አገላለጾችን እንደምሳሌ እናንሳ። የቅርባችን ሰው ስንናገር እየሰማን እንዳልሆነ በተገጋጋሚ ይሰማን “አንተ ደግሞ ሁል ጊዜ አትሰማኝም!” ብለን እናባርቃለን። ይህንኑ ይዘት “ዛሬ እኔ እያወራሁህ እያለው ጥለኽኝ ስትሄድ ለእኔ ሀሳቦች ቦታ የሌለህ እና ትኩረት የማትሰጠኝ አድርጌ ስለወሰድኩት ተናድኛለሁ። ስናገር ጊዜ ሰጥተህ ብትሰማኝ ደስ ይለኝ ነበር። ”

በእነዚህ ሁለቱ አገላለጾች መካከል የሰማይ እና የምድር ያክል ልዩነት አለ። የመጀመሪያው ከሳሽ ነው፤ ጉዳዩን ከቀኑ ክስተት አውጥቶትም ተወቃሽ እና ተከሳሽ አድርጎታል። መቼም እንደ “አንተ ሁሌ” እና “አንተ መቼም” የሚሉ ንግግሮችን መቼም ተጠቅመን ሰላም እንዲወርድ ማሰብ ተላላነት ነው። ውስጣችን አሁን ከሆነው ክስተት የበለጠ የሚንቀለቀል ነገር እንደነበረ እና ሌላውን ለመክሰስ አጋጣሚ እየፈለገን እንደሆነም ተደርጎ ይታያል።

ሁለተኛው የንዴት ገለጻ ከምንም በፊት ንዴቱን የራስ አድርጎታል። መልእክቱ እኔ ተናድአለሁ እንጂ አንተህ አናደድከኝ አይደለም። የተናደድንበትንም ምክንያትም እንዲሁ አስረድተናል። ለወደፊቱም ከዛ ሰው የምንጠብቀውን የወደፊት ለውጥንም ያለ አንዳች መጋፋት መግለጽ ችለናል። ትኩረታችንን በተሰማን ነገር ላይ ማድረግ ነገሩን ወቀሳ እንዳይሆን ያደርገዋል። በግንኙነታችን ውስጥ ያለንን ጥበቃም ያለ አንዳች መጋፋት ማሳወቅ የምንችልበት ዕድል ይሰጠናል። ይኽም ሌላው ሰው ራሱን እንደተጠቃ በማሰብ ወደመከላከል እንዳያዘነብል ያደርገዋል። በሌላ አነጋገር የተሰማንን ስሜት መግለጽ ፍላጎታችንን የመግለጽ መብታችን አካል ተደርጎ ስለሚቆጠርልን ለሌላ ግጭት አይዳርገንም።

ጥንቃቄ

እዚኽ ጋር ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን አንዳንድ ሰዎች ከመጠን በላይ ራስ ተኮር እና የሌላውን ሰው ስሜት መጋራት የማይችሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው። እኚህ በስሜት ቁስላችን ላይ እንጨት በመስደድ የበለጠ ሊያቆስሉን ይችላሉ። ባናደደን ነገር ላይ በመሳቅ እና በማላገጥ ተጨማሪ ስሜታዊ ቁስል ሊፈጥሩብን ይችላሉ። የተናደድነው በእንደዚህ ከመጠን በላይ በራስ ላይ በሚያተኩሩ ሰዎች ከሆነ የሚሻለን በተቻለ መጠን ንግግራችንን እና ግንኙነታችንን የተመጠነ እና የተወሰነ በማድረግ ነው።

ትኩረታችን የእኛ ስሜት ላይ ማድረግ ማለት ግን ንግግራችን ጣፋጭ እና ሌሎች አካላዊ የስሜት መገለጫዎችን ግን የንዴት መገለጫዎች ማድረግ ማለት ግን አይደለም። ከቃላቶቻችን ባሻገር ዽምጻችን እና አካላዊ እንቅስቃሴያችንም መልዕክት እያስተላለፉ መሆኑን መዘንጋት አይገባንም። ፊታችን እና አካላችን እየሸነቆጠ በቃላትችን የቱንም ያክል ብንለሳለስ ሰላምን ከሌሎች ጋር ልናወርድ አንችልም።

ንዴታችን መግለጽ ማለት ግን ምላሻችን በፍጥነት ሁሌ ማሳየት አለብንም ማለት አይደለም። ውስጣችን ገንፍሎ ባለበት ንግግራችን ሚዛናዊ ይሆናል ብሎ ማሰብ ልክ አለመሆኑን መገንዘ ይገባናል። ስለዚህም ከንዴታችን ጋር ተያይዞ ውስጣችን የሚንቀለቀል ነገር ካየን ለራሳችን ጊዜ መግዛት ይኖርብናል። አንድ ታክሲ ውስጥ ተለጥፎ ያየሁትን ንግግር ማስታወስ ይጠቅመናል፣ “ለሚያልፍ ነገር የማያልፍ ነገር አትናገር።” ለራሳችን ጊዜ መስጠት ሁለተኛ እንዳይደግሞ  በእጥፍ ጉዳው እና አጥቃው ለሚለው አሉታዊ ድምጽ ልጓማ ማበጀት በእርግጥም በስክነት ውስጥ ይቻላል። ያኔም ትኩረታችንም ሌላውን ከመጉዳት ይልቅ ከሌላው የምንጠብቀውን ነገር በማሳወቅ ላይ ያተኩራል።

የሰላም እና የእርቅ መንገድ

ንዴታችንን የምንገልጽበት መንገድ ለሌላ ጥል የሚያጋልጠን ወይም ሰላም እና እርቅ የሚያመጣ እንዲሆን በማድረግ ሂደት የእኛው ሚና ከፍተኛ ነው። የሁለቱ ውጤቶች መሠረታዊ ልዩነትም ንዴታችንን ስንገልጽ ትኩረታችን የት ላይ ነው በሚለው ላይ ይወሰናል። ንዴታችን ስንገልጽ ትኩረታችን እኛ የተሰማን ስሜት ላይ፣ የተፈጸመው ተግባር ላይ እና  የተናደድንበትን ምክንያት በማሳየት ላይ ካተኮረ እና ለወደፊት የምንፈልገውን ለውጥ ያለመጋፋት ከጠቆመ መልካም ነው። መልዕክቱም ችግሩ የሰውየው ስብዕና ሳይሆን የተፈጸመው ተግባር ነው ብለን ማመናችንን ያሳያል። ይኽን ማድረግ ንዴታችን ወሰኑን እንዳያልፍ ገደብ ያበጅለታል፤ አንዳችን ሌላችንን የምንረዳበትን መንገድ ይከፍትልናል፤ ለሌላኛው ሰውም ጥበቃችንን በማሳየት በትህትና የምናቀርበው የለውጥ ግብዣ ይሆናል፤ እርቅም የመውረድ ዕድሉም ከፍተኛም ይሆናል።

[1] Gill Bloxham and W. Doyle Gentry. Anger management for dummies (John Wiley & Sons, 2010), 24.

[2] Howard Kassinove,  Anger disorders: Definition, diagnosis, and treatment (Taylor & Francis, 2014), 88.

[3] መዝሙር 44፡9-19።

[4]  Sandra P. Thomas, “Age differences in anger frequency, intensity, and expression.” Journal of the American Psychiatric Nurses Association 8, no. 2 (2002): 44-50, 44.

Share This Story, Choose Your Platform!

Written by : Dr. Tekalign Nega

Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.

Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.

Subscribe To My Page

BE NOTIFIED ABOUT RECENT UPDATES

Leave A Comment