ጸጉረ ልውጥ

በ ዶ/ር ተካልኝ ነጋ (PhD)

የዛሬ ዐሥራ ዓምስት ዓመት ነበር ከአገሬ ኢትዮጵያ ውጭ ለሦስት ወር የአጭር ጊዜ ስልጠና ወደ ህንድ አገር ያቀናሁት። በጉዞዬም  እንግድነትን ለመጀመሪያ ጊዜ ተጋፍጬዋለሁኝ። አዲስ አገር የመጎብኘቱ ደስታ እንዳለ  ሆኖ የእንግድነቱ ስሜቱ ግን ደስ አይልም። “ጸጉረ ልውጥ” መሆን ምቾት ይነሳል። “እኔነቴን እንዳለ ይቀበሉታልን?” የሚል ሥጋት አለበት። እንግዳነት ነገርን ከማድረጋችን በፊት ሁለቴ እንድናስበው ግድ ይለናል። የለመዱትን ነገር ሁሉ እየጠየቁ ቀናትን መግፋት ደግሞ ለውጥረት ይዳርጋል።

በጉዞዬ ብዙ ተምሬያለሁኝ። ወደ ሱቅ ስገባ፣ የአማልክቶች ምስል እና ቅርጽ ስላለ፣ አክብሮት ለማሳየት ጫማዬን ማውለቅ እንደሚጠበቅብኝ በሂደት ተረዳሁ። በየልኳንዳ ቤት ተጥንጠልጥሎ በየቀኑ የማየውን የከብት ሥጋ እዛ የለም። በቀንድ ከብት ቁጥር ከዓለም አንደኛ ብትሆንም የቀንድ ከብቶችን መመገብን ባህሉ አይፈቅድም። የአገሬው ሰው እንኳን ሥጋቸውን ሊበላ ቀርቶ ቀበቶዋቸውን መታጠቅ ይቀፈዋል። ህንድ ስለ ጥሬ ሥጋ ጥፍጥና ማውራት አይታሰብም። ሻይ አዝዤ የቀረበልኝ ሻይ በወተት ነበር። ያላዘዝኩት መጣ ብዪ ስሟገት “ጥቁር ሻይ” ብለኽ መቼ  አዘዝክ በሚል ተወቅሻለሁ። መኪናም የሚነዳው በግራ በኩል ነበርና ራሴን ደጋግሜ ማስታወስ ነበረብኝ። የሀገሩ እሴት፣ አመለካከት እና አደራረግ እኔ ከለመድኩት በእርግጥም የተለየ ነበር።

እንዴት ታየሁ?

ለአገሩ ባዳ ነበርኩ፤ ምድቤ እኛ ውስጥ ሳይሆን እነርሱ ውስጥ ሆኖ አገኘሁት። ሌላነቴን እንዴት አስተናገዱት? ባዳነቴን በጥርጥር ተመለከቱት? ጸጉረ ልውጥ መሆኔ እንደ ችግር ታየ ወይስ ፍቅር አስገኘልኝ? ጸጉረ ልውጥነቴ አብዛኞቹ ጋር ክብር እና እንክብካቤን አስገኘል እንጂ ለጥርጥር አላጋለጠኝም። በየሄድኩበት፣ የማያውቁኝ ሰዎች፣ ይጋብዙኝ እና የሚገርም ቸርነት ያሳዩኝ ነበር። ለባጃጅ የምክፍለው ዝርዝር ሩፔ ሳይኖረኝ ሲቀር ከገዛ ኪሳቸው አውጥተው ሰዎች በተደጋጋሚ ከፍለውልኛል። ህንድ ዝርዝር ማዘጋጀት ያለበት ተሳፋሪው እንጂ እንደ እኛ አገር ባለመኪናው አይደለም።  የማያውቁኝ ሰዎች መንገድ ላይ አይስክሬም ጋብዘውኛል፤ የምፈልገው ቦታ ያለ አንዳች ክፍያ አድርሰውኛል።

ለምን ይህን ሁሉ በጎነት ከማያውቁኝ እና በብዙ ከማልመሳሰላቸው ሰዎች እጅ አየሁ? ስለገረመኝ ጠይቂያለሁኝ። መልሱ ከሂንዲዩዝም አስተምህሮ ጋር ይያያዛል። አማልክት በእንግዶች መልክ ራሳቸውን ሰውረው በሰዎች መካከል እንደሚገለጡ በሂንዲዩዝም ውስጥ ይታመናል። ለምን አማልክቱ ራሳቸውን በሰው መልክ ሰውረው ይገለጣሉ? መልሱ የአማኒያኑን የግብረ ገብ ልክነት ለመመዘን ነው። ይኽም እንግዳን በበጎ ማየትን እና ማስተናገድን የእውነተኛ አማኝነት ሚዛን አድርጎታል።

በእርግጥም የግብረ ገብ ቅኝታችን ትልቁ ሚዛን የግብረ ገባችን ወጥነት ነው፤ ግብረ ገባችን መውደቁ እና መቆሙም የሚመዘነው አይመስሉንም ብለን ለምናስባቸው ሰዎች በምናሳየው መላካምነት እና ቸርነት ነው።  ለሚመስሉን የምናደገውን ቸርነት እና በጎነትማ ሁሉም ያደርገዋል።

ከመጀመሪያው የውጭ አገር ጉዞዬ በኋላም ሌሎች አገሮችን የመጎብኘት ዕድል ገጥሞኛል። ጥቁርነቴ፣ የዶክትሬት ዲግሪዬን የተማርኩበት ኔዜርላንድ ውስጥ፣ አንዳንድ ነጮች (በቁጥር ጥቂት ናቸው) ጋር በጥሩ አልታየም።  ከሱፐር ማርኬት ስወጣ የሆነ ነገር አንስቶ ቢሆንስ በሚል ጥርጣሬ የሌላው ሰው ሁሉ ቦርሳ እንዳች ሳይነካ የእኔ ግን ከማልፍበት ማሽን ባለፈ በእጅ ተብጠርጥሮ ተፈትሾ ያውቃል።  እኔም “የምትፈልገውን ነገር አገኘህ?” በሚል ፈገግታም አልፌዋለሁኝ። ለእነዚህ የጥበቃ ሠራተኞች ሌላነቴ፣ ጥቁርነቴ፣ እንደ ሌባ እንዲጠረጥሩኝ አድርጎኛል፤ የምንጎራደድበት ሸቀጥ አከባቢም ያለምክንያት ደጋግመው ሲንጎራደዱም ታዝቤያለሁኝ።

እኛስ?

የእኛው ሀገር ዜጎች ደቡብ አፍሪካ የሆነባቸውንም ከትውስታችን መቼም የምንረሳው አይደለም፤ እንግዶች መጥተውብናል ደግሞም ሀብታችንን እና ዕድላችንን ተሻምተዋል በሚል የደረሰባቸውን ዘግናኝ ክስተቶች እናስታውሳለን። እዚሁ አገሬም ይሄነው የሚባል እንከን በገቢር ያላገኙባቸውን ነጮች  እኛን ስለማይመስሉ አናምናቸውም። ከነጮች ጋር በመሠረትኳቸው የልብ ወዳጅነት ውስጥ የሚቀርቡኝ “አትመናቸው” ብለው በተደጋጋሚ መክረውኝ ያውቃሉ። ለብዙዎች አሁንም ድረስ “ነጭነት” ሰላይነት ተደርጎ ስለሚታይ የልብ ጉዳይን የምናካፍላቸው አይደሉም። አብሬያቸው ታክሲ ብንሳፈር ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በማስከፈል ሂደት ውስጥ እድንተባበር ከሀገሬው ሹፌር በተደጋጋሚ ተጠይቄ ደግሞም ባለመተባበሬም ተወቅሼም ተሰድቤም አውቃለሁ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጤናቸው በሚል ለበርካታ ዘመናት በመካከላች የኖሩ የሌላ ብሄር አባላት ላይ ያደረስናቸውን ጭከናዎች እና በደሎችን እንዲሁ ከማናችንም ትውስታ መቼም የሚጠፉ አይደሉም። በሌላ ሰው ላይ እንዴት ያን ያክል ይጨከናል የሚባሉ ግፎችን ፈጽመናል። ከቀያቸው በርካቶች ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ተዘርፏል ወድሟል፣ ክቡሩ የሠው ሕይወት በጭካኔ ተቀጥፏል።

ብሂሎቻችንስ ምን ይጠቅሙናል? እንግድነት ከዝምድናስ ጋር አጣምረው ያቀርቡልናል። “ዘመድ ከዘመድ አህያ ካመዱ” የሚለው ምን ይነግረናል? ቢጤያችንን ወይም የሚመስለንን ማግኘትን የሚያበረታታ አይደለምን?ለምንድን ነው የሚመስለንን መፈለግ ያለብን የሚለውን አሰላስሎም “ዛፍ ሲወድቅ ከግንዱ ሰው ሲቸገር ከዘመዱ” እንባላለን። ነገሩ ለችግር ጊዜያችን የሚደርስልን ዘመዳችን መሆኑን የሚያሳስብ ነው። ዝምድናችን አንዳንዴ በጥቅም ላይ እንደሚመሠረት ለማሳየትም “ያለው ዘመድ አለው” ይባልል። ዝምድና ጉርብትናም መሆኑን ለማሳየት “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት” የሚል ብሂልም አለን። ዝምድናም ሊቆራረጡት የሚችሉት ነገር መሆኑን ለማሳየትም “ሚስት ከፈቷት ባዳ ማሽላ ከተቆረጠ አገዳ” ይባላል። እነዚህን አባባሎች ብቻ ብናሰላስላቸውም ብዙ የሚሉን ነገር አለ። ዝምድና ትሥሥር እና ቅርርብ መሆኑን ይነግሩናል፤ ከሚመስሉን ጋር እንደምንዛመድም ይነግሩናል። ዝምድናችን ጥቅም ፈላጊነት ሊኖርበት እንደሚችልም ያሳዩናል። ባዳነትም ትሥሥር ማጣት እና ልዩነት መሆኑንንም ያሰምሩታል።

እንግዳነት

እንግድነት የቁሳዊ ቦታ ጉዳይ ብቻ አይደለም። በአብዛኛውም እንደውም ማኅበራዊ ነው።  እንግድነት ባዳነት ነው። እንግድነት በልዩነት ላይ ተመስርቶ የእኛ አካል አይደለም ወይም አትመስለንም ተብሎ መበየን ነው። እንግድነት የእኛው ብዙ ተመሳሳይነት ወደ ጎን ተትቶ ጥቂቱን ልዩነት የማጉላት ነው። እንግድነት ሌላነት ነው፤ ሌላነቱም ደግሞ በአብዛኛው በበጎ የሚታይ አይደለም። እንግድነት ለሌላው የሚሰጡ መብቶችን መከልከያ መሳሪያ እንጂ ማቀፊያ አይደለም። እንግድነት በአብዛኛው መጠርጥር እና በሥጋት መታየት ነው።  እንግድነት በልዩነት ምቾች ማጣት ነው። የአለመሳሰሉ ዝርዝር ልዩ ልዩ ሊሆን ይችላል። የተለየነው በብሄራችን፣ በቆዳችን ቀለም፣ በምንከተልው ኃይማኖት፣ በምንከተለው የፓለቲካ ርዕዮት፣ በባህላችን፣ ጾታችን፣ ማኅበራዊ ደረጃችን  ሊሆን ይችላል።

የሕይወታችን ጤናማነት እውነተኛው መለኪያውም እንግዳን የምናስተናግድበት መንገድ ነው። እንግዳን መቀበል የእኛ ነው የምንለው ሥፍራ ሌሎች የምንላቸው ለማስገባት እና በቸርነት ለማስተናግድ መፍቀድ ነው። በሌላ አገር ጉብኝቴ በተቀበሉኝ እና እንደ ሥጋት እንግድነቴን በተመለከቱት መካከል ያለው ልዩነት ሌላነትን ካዩበት አተያይ ጋር ይያያዛል። ሌላነቴን እንደ አምላክ መገለጥ የተመለከቱት ሊያገለግሉኝ ተረባርበዋል። እንግዳነቴን፣ ቀርበው ሳያውቁኝ፣ እንደ ችግር የተመለከቱት በዐይነ ቁራኛ እንዲከታተሉኝ አድርጓቸዋል።

ልበ ሰፊነት

እንግድነቴነቴ በበጎ የተመለከቱትን ሰዎችን አንዳች ነገር ብማርባቸው በሚል ስሜት ላጤናቸው ጥሬያለሁኝ። የሚያመሳስላቸው ነገር የልባቸው ስፋት ነው። የልባቸው ስፋት ለእኔ ለእንግዳው ልባቸው ውስጥ ቦታ አዘጋጅቶልኛል። ቅኝታቸው እኔን ለማወቅ እንጂ ለመፈረጅ አይደለም። ጠያቂዎች ናቸው፤ ልዩነቶችን ያደንቃሉ፤ ለልዩነቶች አክብሮትም አላቸው።  ወደ ቁሱ ቤት ተጋብዤ የተትረፈረፈ ነገር ቀርቦልኝ እንዳልተቀበሉኝ የተሰማኝ ቦታዎች አሉ። እኔ አለኝ ከምለው ተስተናግጄ ልቤም ያረፈባቸው ቦታዎችም አሉ። ይኽ እውነትም እንግዳን መቀበል በታዛችን ሥር ከማስገባት እና ማዕድ ከመቋደስ በበለጠ በልባችን ውስጥ ሥፍራን ማዘጋጀት መሆኑን እንድረዳ አድርጎኛል።

እንግዳ በልባችን ውስጥ ሥፍራ ሲያገኝ  አብሮነት አይቸግረንም። አብረነው ማውጋት፣ መጨዋወት እና ማሰላሰል እንችላለን። ደስታው ደስታችን የሚያስለቅሰው ነገር ዕንባችን ይሆናል። ግንኙነታች የእበልጣለሁ ውድድርም አይደለም። ልዩነቱ ሌላ ውበት ሆኖ ይታየናል እንጂ ምቾት አይነሳንም፤ ሌላውን ለማወቅ የማይነጥፍ ጉጉት አለን፤ አንዳች ነገር እማርበታለሁ በሚል የምናደምጥበትም ጆሮ ይሰጠናል። ስለማይመስለኝ በጥርጥር እና በሥጋት አየዋለሁኝ የሚለው የብዙዎቻችን ቅኝት እኛነታችንን አይገዛም፤ ማካፈልም አንቸገርም።

እንግዶችን፣ የማይመስሉንን፣ እንዴት እያየን ነው? ልዩነታቸው ይማርከናል ወይስ ያርቀናል? ልባችን ክፍት ነው ወይስ ዝግ? እንግዳን በመቀበልስ እንተጋለን? ለቅርባችን የምናሳየውን ነገር እና በጎነት ለእንግዶች ለማካፈልስ ዝግጁነት አለን? እንግዳ የምንኩራራበት ማንነታችን እውነተኛነት መፈተሻ እና መፈተኛ ሥፍራ መሆኑን አውቀናልን?  እንግዳችንን የስውሩ አምላክ መገለጥ መሆኑን እናስባለን? “የእግዚአብሔር እንግዳ አያድርም ከሜዳ” የሚለው ቀደምት ብሂላችን በፍቅር እና በደስታ ሌሎችን እንድቀበል እያደረገን ነውን? ለእንግዶች በልባችን ሥፍራ በማዘጋጀታን፣ ልባችንን በማስፋታችን፣ ያለንን በማካፈላችን እናተርፋለን እንጂ አንከስርም።

Share This Story, Choose Your Platform!

Written by : Dr. Tekalign Nega

Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.

Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.

Subscribe To My Page

BE NOTIFIED ABOUT RECENT UPDATES

2 Comments

  1. Medi March 20, 2025 at 3:58 pm - Reply

    Amazing! blessings for sharing!

  2. Betel Tagesse March 25, 2025 at 1:43 pm - Reply

    It is a great message. We are advised to welcome others in our home. I can see these strangers can be God sent. God bless you!

Leave A Comment