
ጥሩ ሕይወት
በ ዶ/ር ተካልኝ ነጋ (PhD)
እከሌ ወይም እከሊት “ጥሩ ሕይወት” ይኖራል ወይም ትኖራለች እንላለን። “ጥሩ ሕይወትን” እንደ ግብ አንግበንም “ለጥሩ ሕይወት” ሁላችንም እናቅዳለን፤ እንሠራለንም። “ጥሩ ሕይወት” የምንለው ነገር ግን ምንድን ነው? “የጥሩ ሕይወት” ምልክት ከሀብት፣ ሀብት የሚያስገኘውን ምቾት ከማጣጣም እና ከዝነኝነት ጋር ተቆራኝቷል። የሰዎች የጥሩ ሕይወት ደረጃም ከሚቆጥሩት የረብጣ ገንዘብ መጠን፣ ተንፈልሳሰው ከሚምነሸነሹበት የመኪና ሞዴል እና አንገታቸውን ከሚያስገቡበት የባለ ብዙ ክፍሎች ቤት ውበት፣ እና ዝናን ተከትሎ ከሚታጠኑት ውዳሴ ጋር ተያይዟል። በእርግጥ ጥሩ ሕይወት ሚዛኑ ሀብት እና ዝና ነውን?
ሥነ ልቦናችን?
ጥናቶችስ ምን ይላሉ? በሀገረ አሜሪካ የሚሊኒየም ትውልድ ተብለው በሚታወቁት ወጣቶች ላይ በ2007 የተሠራን ጥናትን በዋቢነት እናንሳ። ጥያቄው “በሕይወታችሁ ቅድሚያ የምትሰጡዋቸው ግቦች ምንድን ናቸው የሚል ነበር?” ከ100 መካከል 76 “ባለጸጋ መሆን” የመጀመሪያ ግባችን ነው ብለዋል። ከ100 ውስጥ 50ዎቹ ደግሞ ዝነኝነትን ከዋንኛ ግቦች ተርታ ሰድረውታል። እርግጥ ነው ከ10 ዓመት በኋላ እነዚሁ ተጠያቂዎች ዝነኝነትን ከደረጃዎቹ ዝቅ አድርገውታል። ባለጸግነትም ቢሆን መለዘቡ አልቀረም። ገንዘብ መሥራት፣ የሥራ ስኬት እና ከዕዳ ነጻ መሆን ቀዳሚ ተፈላጊዎች ሆነው ቀጥለዋል። 1 እኚህ አሀዞች ምን ይነግሩናል? ሀብት እና ዝነኝነት በተለይ ወጣቶች ጋር እጅግ የሚፈለጉ የሕይወት ግቦች መሆናቸውን እንረዳለን።
ዋንኛ የምንላቸው ግቦች ደግሞ ሌሎች ግቦችን መሥዋዕት እንድናደርጋቸው ያደርጉናል። ገንዘብ ማከማቸት ዋንኛ የሕይወት ግባችን ሲሆን የሕይወት ንጽህና ዋጋ የማንሰጠው ስለሚሆን ቅኝታችን “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” ይሆናል፤ እናግኝበትን እንጂ የትኛውም መንገድ ልክ ይሆናል። የሕይወት ግባችን ዝነኝነት ሲሆን ማስመሰል ችግር መሆኑ ያበቃል፤ የአደባባዩ እና የጓዳው ሕይወታችን ለየቅል መሆኑም አይረብሸንም፤ ሕይወታችንን እውነት ሳይሆን ማስመሰል ይሆናል፤ ሌሎች ይቀበሉን እንጂ ከህሊናችን ሆነ ከአምላክ ጋር መጣላቱ ችግር መሆኑ ያበቃል።
ይኽ አስተሳሰብ የቱን ያክል ሥነ ልቦናችንን እንደገዛን ለማሳየት ሌላ ጥናት ላንሳ። በአዕምሮ ላይ የተደረጉ ጥናቶች የምናጣጥመው የእርካታ መጠን የሚመዘግበው የአዕምሮዋችን ክፍል (medial orbitofrontal cortex) መሆኑን አሳይተዋል። ደስታችን በጨመረ ቁጥር በዚህ የአዕምሮዋችን ክፍል የሚታየው እንቅስቃሴው ይጨምራል። በዚኽ የአዕምሮ ክፍል ላይ በተደረገ ጥናት፣ የምንጠጣው ወይን አንድ ዓይነት ሆኖ ሳለ፣ ወይኑ ውድ ወይም ርካሽ ነው ተብሎ የተነገረንን ማመናችን ብቻ በእርካታችን ላይ የሚያደርሰው የራሱ ተጽእኖ እንዳለው አመላክቷል። ሰዎች ውድ ወይን እንደተጎነጩ ሰዎች ባሰቡ ቁጥር እርካታቸው ይጨምራል፤ ርካሽ ወይን እየጠጡ በተሰማቸው ቁጥር ደግሞ እርካታቸው ያንሳል። 2 ይኽ ምን ያመለክተናል? ሥነ ልቦናችንም ማኅበራዊውን አተያይ የእርሱነቱ አካል አድርጎ መቀበሉን ያሳያል።
ሐይማኖታችንስ?
አገራችን የሐይማኖተኞች ምድር ስለሆነች ሥነ ልቦናችንን ከሐይማኖት አስተምሮት አንጻር እንፈትሽ። የሙስሊሞች የመጨረሻው ነቢይ የሆኑት መሀመድ “ሀብት ብዙ ንብረት በመያዝ አይደለም፣ እውነተኛ ሀብት ግን በነፍስ ውስጥ እርካታ ሲሰማን ነው።” 3 ማለታቸው ተአማኒነት ባላቸው ሀዲሶች ተዘግቧል። የነቢዩ መልእክት ግልጽ ነው፤ እውነተኛ ሀብት የነፍስ እርካታ እንጂ ያከማቸነው ሀብት አይደለም። የክርስትና እምነት ጀማሪ እና ፈጻሚው ኢየሱስ ክርስቶስም “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል?” ሲል ጠይቋል። 4 የኢየሱስ መልእክትም ዓለም እና ምቾቱ ተደማምረው ነፍስ ካላት ዋጋ ጋር አይወዳደሩም እና ዋንኛው ጉዳይ የነፍስ ጉዳይ መሆን አለበት የሚል ነው።
አይሁዱ ጠቢቡ ሰለሞንም ሀብት ብቻውን ከንቱ መሆኑን “ እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል። የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል።” ሲል ገልጾታል። 5 እንዲህ ዐይነት ትምህርቶች ምን ያሳዩናል? የባላጠጋውን ምሳሌ ያስታውሱናል። ባለጠጋው ክምችቱን ተመልክቶ “አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ።” 6 ብሏታል። የባለጠጋው ቅኝት ግልጽ ነው፤ ክምችቱ የተፈለገው ለዕረፍት እና ለደስታ ነው። እስልምና፣ ክርስትና እና ይሁዲነት አጽኖት የሚሰጡት ገንዘብ እና ዝና በራሳቸው ችግር ባይሆኑም የጥሩ ሕይወት መመዘኛዎች ፈጽሞ አለመሆናቸውም ያንኑ ያክል ግልጽ ነው። በእርግጥም በሐይማኖቶቹ አስተምህሮ “ነፍስ ከመብል ሰውነትም ክልብስ ይበልጣልና።”
ለምን?
ገንዘብ ለምን ይኽን ያክል ተፈለገ? መልሱ ግልጽ ነው፤ ገንዘብ በራሱ እርባና ያለው ነገር ስለሆነ አይደለም። ጭው ያለ በረሃ ውስጥ ብቻችንን የቱንምም ያክል ገነዘብ ብንታቀፍ አንዳች አይረባንም፤ የውሀ ጥማችንን እንኳን አይቆርጥልንም። ገንዘብን ትልቅ ቦታ የሰጠንበት ምክንያት በምንኖርበት የልውውጥ ዓለም ውስጥ ገንዘብ ፍጆታዎቻችን ማሟያ መንገድ ሰለሆነ ነው ። ገንዘብ መለዋወጫ ባይሆን ኖሮ ማንስ ይፈልገው ነበር? የዕለት ጉርሳችንን ባያስገኝልን፣ ዕፍረት ሥጋችንን የምንሸፍንበት ዕራፊ ጨርቅ ባይገዛልን፣ ባንዝናናበት፣ ቁስ እና አገልግሎት ባንገዛበት የትስ እንሻው ነበር? ገንዘብ የተፈለገበት ምክንያት ፍላጎቶቼን ያሟላልኛል በሚል ነው።
ዝነኛነት? ዝነኝነት በብዙ ሰዎች መታወቅ አይደለምን? የዝነኝነት ፍላጎታችንም ከሰው ማኅበራዊነት ጋር የተቆራኘ ነው፤ ብቻችን ሆነን ማጣጣም የማንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉን፤ አብሮነትን የመፈለጋችን ማሳያ ነው። ለዚህም ነው ዘላቂ ማኅበራዊ መነጥልም በሥነ ልቦናው መስክ እንደ ችግር የሚወሰደው፤ ማኅበራዊነታችን ሰዎችን እና አስተያየታቸውን እንድንሻ ያደርገናል። ዝነኝነት ፍለጋው ዝነኛ መሆን ብቻ ሲሆንስ? በሌሎች ሰዎች ልብ ቦታ ለማግኘት የሚደረግ ከንቱ ሩጫ ይሆናል፤ ቅኝቱም ለሌላው ግድ የሌለው እኔነት ይታይበታል። የእንዲህ ዐይነቱ ሩጫ ችግሩ በሌሎች ልብ ቦታ ማግኘት ደግሞ የሌሎች ሰዎችን ተለዋዋጭ ጥበቃ ሁል ጊዜ ማሟላት መጠየቁ እና እኛንም ለማያስፈልግ ውጥረት ማጋለጡ ነው፤ ዛሬ ልባቸው ያኖሩን ሁሌም ልባችን እንዲያኖሩን መታተር ሕይወታችን ይሆናል፤ ሂደቱም አድካሚ ነው።
እናሳ?
ባለጠግነቱም ሆነ ዝነኝነቱም ሰዋዊ ፍላጎቶች ከሆኑ ምን እናድርጋቸው? ይኽን ጥያቄ በመመለስ ሂደት ፈላስፋውን ኢፒኩረስን ማሰብ ይጠቅማል። ኢፒኩረስ ሰዎች ለፍላጎቶቻችን ሁሉ ባሪያ መሆን እንደሌለብን ይመክራል፤ ማኅበረሰባችን የጫነብንን እና የሚያሻሽጥልንን ነገር ሁሉ ሳንመረምርም ልንቀበለው አይገባም። ይኽ ደግሞ ፍላጎቶቻችንን መመርመር እና በተገቢው ማስተዳደርን ይጠይቃል።
ተገቢውን ፍተሻ ለማድረግ እንዲረዳንም ፍላጎቶችን ኢፒኩረስ ሦስት ቦታ ከፍሏቸዋል። እነዚኽም፦ 1) ተፈጥሮዋዊ እና አስፈላጊ፣ 2) ተፈጥሮዋዊ ግን የማያስፈልጉ፣ 3) እና ከንቱ ወይም ባዶ ፍላጎቶች ናቸው። ተፈጥሮዋዊ እና አስፈላጊ በሚለው ምድብም ያለ እነርሱ ትርጉም ያለው ሕይወትን መምራት የማንችልባቸው እንደ ምግብ፣ መጠለያ ያሉትን ማሰብ እንችላለን። ተፈጥሮዋዊ ግን የማያስፈልገው በሚለው ምድብ ጊዜያዊ እርካታን የሚስጡ ነገር ግን ለወደፊት ለህመም የሚያጋልጡን ከመጠን ያለፈ ደስታን እና ምቾትን የመውደድ ፍላጎቶችን ልናነሳ እንችላለን።ውድ ነገርን መፈለግን በዚህ ምድብ ውስጥ ልናካትተው እንችላለን። ባዶ እና ከንቱ ፍላጎቶች በሚል የተገለጹት ደግሞ የዝነኝነት፣ የኃያልነት እና የብልጽግና ፍላጎቶች ናቸው። 7
ለፈላስፋው ባዶ ወይም ከንቱ ፍላጎቶቻችን ከታመመ ማኅበረሰብ የወረስናቸው ፍላጎቶች እንጂ ተፈጥሮዋዊ ፍላጎቶች አይደሉም፤ ለፍላጎቶቹም ማብቂያም የላቸውምና የሆነ ቀን ልናስቆማቸውም የምንችላቸውም አይደሉም። ሌላኛው ችግራቸው እኚህ የበርካታ አላስፈላጊ ፍክክሮቻችን፣ውጥረታችን፣ እና ግጭቶቻችን ምንጮች በመሆናቸው ነው። እነዚህን በማሳደደም እውነተኛ ዕረፍት እና እርካታን አናገኝም፤ ሕይወታችን የማይሞላ ጉድጓድን ለመሙላት የሚደረግ ጥረትን ይመስላል።
እንደምናስበውም ያማረንን ሁሉ መግዛት መቻላችን እውነተኛ እርካታን አያስገኝልንም። ለዚህም ነው በሥነ ልቦናው መስክ “ደስተኛ ያልሆኑ ሀብታሞች” እና “ደስተኛ ድሆች” የሚል ጽንሰ ሀሳብ “ደስተኛ ሀብታሞች” እና “ደስተኛ ያልሆኑ ድሆች” ከሚለው ማኅበራዊ አስተሳሰብ ጋር በንፅፅር የደረጀው። በእርግጥም ድሆች ሁሉ ደስታ የራቃቸው እና ሀብታሞች ሁሉ በደስታ የሚራጩ አይደሉም። “ደስተኛ ያልሆኑ ሀብታሞች” እና “ደስተኛ ድሆች” መኖራቸው ደስተኛነት ተጨባጭ ሚዛን ብቻ ሳይሆን ከግላዊ ሚዛናችን ጋርም የመያያዙን እውነታ ያመላክታል። ደስተኛ ድሀ በማያመች ሕይወት ውስጥ እየኖረ ደስተኝነት የሚያጣጥም ሲሆን ደስታ የራቀው ሀብታም በምቾት እየተቀማጠለ ደስተኝነት የራቀው ነው። ይኽ እውነትም የሕይወታችን ትርጉም ሆነ እርካታ ካከማቸነው ሀብት ጋር ቀጥተኛ ተዛማጅነት እንደሌለው ያመለክተናል።
ሀብት ከደስተኛነት እንድንርቅ መንገድን የሚከፍተው ዕይታው ቁሳዊነት ሲሆን ነው፤ እኛነታችን የእኛ ነው ከምንለው ቁስ ጋር ለመለየት ሁሉ የሚያስቸግር ይሆናል፤ ቁሱን ዋንኛ ነገር በማድረግም የሕይወት ዋንኛ የሆኑ ነገሮችን ችላ እንድንላቸው ያደርገናል፤ ሀብት መጠቀሚያ መሆኑንም እንዘነጋለን። ቁሳዊነት ደግሞ ሦስት ዐይነተኛ መገለጫዎቹ አሉት። እነዚህም ቅናት፣ ቸር አለመሆን እና ሁሉን የራስ የማድረግ ፍላጎት ናቸው። ስንቀና ሌሎች ያላቸውን ነገሮች ለራሳችን ማድረግን እንሻለን፣ ስንስገበገብ የራሳችንን የሆነ ማንኛውንም ነገር ማካፈል አንፈልግም እና ቸርነት ይቸግረናል፣ ያለን የሚጎድል ይመስለናል ደግሞም ተጨማሪ ማግበስበስ ቅኝታችን ይሆናል። 8 ስለዚህም፣ ቅናት እናስወግድ በሌሎች ስኬትም ደስ ይበለን፣ ያለንን በማካፈል በመስጠት ውስጥ ያለውን እርካታ እናጣጥም፣ ያለንን እናጣለን በሚል ሥጋት የተቀፈደድን የቁስ እስረኞች አንሁን።
የታዋቂነቱ ፍለጋ ደግሞ በመኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ አዎንታዊ ነገርን ከመጫወት በተፋታ ቁጥር የእኛው የአዕምሮ ጤና ጭምር አደጋ ውስጥ መውደቁ አይቀርም።ስለምንስ ራሳችንን የማያስፈልግ ውጥረት ውስጥ እንከታለን? በሰው ፊት ተቀባይነት እንደምንፈልገው ሁሉ ከህሊናችንም ሆነ ከአምላክ ጋር ሰላምን እናውርድ። ለሰው ብቻ መኖራችንን እናቁም። ይልቁኑ ዝነኝነታችን በመኅበራዊነት ውስጥ አዎንታዊ ሚናን ከመጫወት ጋር ይቆራኝ። ዝነኝነታችን ለፍትህ እና ለእኩልነት ታጋይ ያድርገን። ለሁሉም ሰው የምንሰጠውን ዋጋ እኩልነት እንዳያቃልልም እንትጋ።
[1] Robert Waldinger and Marc Schulz.The Good Life: Lessons from the World’s Longest Scientific Study of Happiness (New York: Simon & Schuster, 2023), 1.
[2] Jonah Lehrer, How we decide (Houghton Mifflin Harcourt, 2010), 148-149.
[3] Sahih al-Bukhari 6446
[4] ሉቃስ 9፡25፣ ማር 8፡36፣ ማቴ 16፡26
[5] ምሳሌ 15፡16-17
[6] ሉቃስ 16፡19
[7] Tim O’Keefe, Epicureanism. (New York: Routledge, 2014), 123-127.
[8] Aaron Ahuvia, and Nancy Wong. “Materialism: Origins and implications for personal well-being.” European advances in consumer research 2, no. 1995 (1995): 172-178.
Written by : Dr. Tekalign Nega
Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.
Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.

