በሐይማኖቴስ  አትምጣብኝ!

በ ዶ/ር ተካልኝ ነጋ (PhD)

አሁን ላይ፣ በተለይ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ ከመቼውም በበለጠ ደጋግመን የምንሰማው ድምጽ “በሐይማኖቴስ አትምጣብኝ!” ሆኗል። “አትምጣብኝ!” ለስላሳ ንግግር ሳይሆን ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ነው። ማስፈራሪያም በውስጡ አዝሏል፤ ነገሩ ውርድ ከራሴ ነው። መልእክቱ በብዙ ነገር እታገስሀለው በሐይማኖቴ ከመጣህብኝ ግን በፍጹም አልታገስህም ነው።  ምላሼ የቱንም ያክል ዋጋ ቢያስከፍለኝም አልምርህም ነው። ሐይማኖት በእርግጥም ለአብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያን ስስ ብልታችን ነው፤ ስቀን የምናልፈው ነገር አይደለም፤ ሐይማኖታችን ሲገፋ በትዕግስት መስማቱም ከአምላክ ጠላቶች ጋር መተባበርም የሚመስለንም ጥቂት አይደለንም።

ለምን?

እኛ አገር ሐይማኖት እና ሐይማኖተኝነት በእርግጥም ለዘመናት ስናወድስ ኖረናል።  ሐይማኖት በማኅበረሰባችንም ካገኘው እጅግ የከበረ ሥፍራ የተነሳም አንዳንዴ መታበያ እና መከበሪያም ሁሉ ይሆናል፤ ሐይማኖተኛ መባልም እንወዳለን። 1 እንደ እኛ ሐይማኖተኞች አይደሉም የምንላቸውን ኢአማንያንን ለመጠየፍም አገልግሏል፤ እንደኛ የማያጠብቀውም የእኛው ወገንም ቢሆን በንቀት ከላይ ወደታች እንመለከተዋለን። ለዘመናት ውዳሴ የጠገበ እና አይነኬ የነበረ ማንኛውም ነገር ሁሉ ትችትን ማስተናገድ የሚችልበትን ጥንካሬ እንደማይኖረው ደግሞ የታወቀ ነው። ስለዚህም በሐይማኖታችን ላይ የሚደርስ ማንኛውም ትችት በቶሎ ቱግ ያደርገናል።

አሁንስ? ነገሮች ቀሰ በቀስ እየተለወጡ ነው። ምዕራቡ ዓለም የደረጀው የሰላ ትችት እና ስላቅ ሐይማኖት እና ሐይማኖተኝነት ላይ መሰንዘር ተጀምሯል፤ በሐይማኖቱ መንደር ያለንም ጎራ ለይተን እርስ በእርሳችን መተካተኩን እና አንዳችን በሌላችን ላይ መሳለቁን ተያይዘነዋል። “በሐይማኖቴስ አትምጣብኝ” ለሚል ለእኛ ዐይነቱ ሐይማኖተኛ ሕዝብ ደግሞ መተቻቸቱ ፈታኝ ነው፤ ለሌላ መቋሰል ይዘጋጀናል።

እየተሰነዘሩብን ላሉት ትችቶ የእኛ የሐይማኖተኞቹ ምላሽ ውስጥ ጎልቶ የሚሰማው ዽምጽ ግን ምንድን ነው? በእኔ መልከታ ትችቶቹን “በይሆንን?” መንፈስ ከማድመጥ ይልቅ ትችቱን መልሶ ወደመተቸት አብዛኞቻችን እናደላለን። አንዳንዶቹ  ትችቶቹ ልክ መሆናቸውን ህሊናችን እየመሰከረብን ሁሉ ትችቶቹን መቀበል ይቸግረናል። በሐይማኖታችን ላይ የሚደርስን ትችት በበጎ መመልከትም ራስን ማሳነስ የሚመስለን ጥቂት አይደለንም።

ትችቶች የሚወልዱት የሚበልጥ ትችትን  እንጂ መደማመጥን ካልሆነስ? ውጥረት ላላጠራት ምድራችን ተጨማሪ ችግር ማቀበላችን አይቀርም፤ እያቀበልንም ነው። በዚህ መጣጥፍ ውስጥ ሐይማኖታችን ሲተች እንዴት እናድምጥ የሚለውን አብረን እንጠይቃለን። በሐይማኖት እና በሐይማኖተኞች ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶቹን ተቻኩለን ግብረ መልስጥ ከመስጥታችን በፊት በልበ ሰፊነት ብናደምጥስ ምን እናተርፋለን የሚለውንም አብረን እናሰላስላለን።

አይተችም!

ከሐይማኖት ጋር ተያይዞ ትችትን በአዎንታዊነት የማስተናገድ ነገር ሲነሳ የሚረበሹ አማኞች በቁጥር ጥቂት አይደሉም። የዚህ ዓይነተኛው ምክንያትም አብዛኞቻችን ሐይማኖትን በቅርጹ ውበት እንጂ ከኑሮዋችን ጋር ባለው ገቢራዊ ተዛምዶ ስለማንፈትሸው ይመስለኛል። ስለዚህም ሐይማኖታችን እና ሕይወታችን ለየቅል ተፋተውብናል። የሐይማንኖታችንን በጎ ተጽእኖ ሳይሆኑ ቅርጹን እያየን ስንደመም፣ ራሳችንን እንደ ዕድለኛ ስንቆጥር፣ እና ከእኛ ውጭ ናቸው ለምንላቸው ደግሞ በሀዘኔታ ከንፈር ስንመጥ እንታያለን። ከማመናችን የተነሳ እኛ በምን ከሌሎቹ በዕለት ተዕለት ምልልሳችን ተሻልን የሚለውን ግን አብዛኞቻችን ዘንግተነዋል።

ሐይማኖታችን  ግን መመዘን ያለበት በቅርጹ ወበት ብቻ ነውን? ከቅርጹ ባሻገር በሕይወት መንገዳችን ላይ ባሳደረው በጎ ለውጥ ሐይማኖተኝነታችን መለካት የለበትምን? ሐይማኖት በተጽእኖው ጭምር ካልተመዘነ ከሌሎች ውብ ሰዋዊ ፍልስፍናዎች በምንስ ይለያል? ሐይማኖታችን በአብሮነት ከምንሰበሰብባቸው ከጁማ እና ከሰንበት ቀናት ባሻገር በእኛ ላይ ባመጣብን በጎ ተጽእኖ ጭምር መገምገም አለበት። ሐይማኖት በእርግጥም ሁላችንም ሐይማኖተኞች ከምንለው በአዕምሮዋችን ከምናስባቸው ከሌሎች በጎ ሀሳቦች የሚልቅ ከሆነ በእኛነታችን ላይ ባሳደረው ጉልህ ተጽህኖ መነጽርም ጭምር መፈተሽ አለበት። አሊያማ እኛ ሐይማኖተኞች የማንኖረውን የምንናገር ግብዞች እንሆናለን፤ ግብዝነትን የሚያጸድቅ ሐይማኖት ደግሞ ማናችንም የለንም። ተናጋሪ በበዛበት በአሁኑ ዓለም ውስጥም በመናገር ብቻ በልዩነት የምንቆም እና የአምላክ ምስክር የምንሆን ከመሰለንም ራሳችንን እናታልላለን።

ሐይማኖታችን አይተችም የምንል መመኪያችን ምንድን ነው? ነገሩ ሐይማኖትን በየእምነት ተቋሞቻችን በጋራ ተሰባስበን የምንፈጽማቸው ከበራዎች ቅዱስነት እና ልክነት ብሎም  ምስባኮቻችን ላይ ከሚፈተተው የአምላክ ቃል ልክነት ጋር ብቻ ከማያያዛችን ጋር ሳይተሳሰር አልቀረም። ሐይማኖታችን በሕይወት መንገዳችን ላይ ባደረሰው በጎ ተጽእኖ ጭምር ሲፈተሽስ? ማናችንም የተኩራራንበትን ያክል የሚያኩራራ ነገር እንደሌለን ይገባናል፤ በሌላው ላይ የምንጠቋቀመውን ክፉ ነገር መልኩን ለውጦ እኛው መካከል መንሰራፋቱን መመልከትም አይቸግረንም።

ትችቶችን በበጎ ስለማንመለከትም በትችቶች እየተሻሻልን አይደለም። ትችቶችን በትክክል ብንሰማ ትችቱን አምላክ ተሰደበ በሚል ሳይሆን የምንሰማው ከእኛ የተነሳ አምላካችን ተሰደበም በሆነ ነበር። ከእኛ የተነሳ አምላክ ተሰደበ ካልንም ንሰሐ ገቢዎቹ እኛው እንሆናለን፤ መንገዳችንንም አስተካክለን የኑሮ ምስክሮች እንሆነዋለን እንጂ በአምላክ ስም ሌላ ጠላት ፈጣሪዎች አንሆንም። አሁን ላይ ያለው ትልቁ ችግርም እንዴት ተሰደብን እንጂ ምን አምላካችንን አሰደበው አይደለም። የዚህ ዐይነተኛው ምክንያትም  ሐይማኖትስ በጋራ የምንሰበሰብበት የጁማ ወይም ሰንበት ቀናት በምንፈጽማቸው ተግባራት ብቻ መሳላችን ነው። በምንኖረው ሳይሆን በምንናገረው ራሳችንን መመዘናችንም  ኑሮዋችንን ከመቼውም የበለጠ የግብዝነት አድርጎታል፤ ጉድለታችንንም ተመልክተን ለማስተካከያው እንዳንሠራ  አድርጎናል።

ለነገሩ የሐይማኖተኞቹ መንገዳችን ብቻ ሳይሆን ሐይማኖታች ቅርጹ ጭምር ችግር ሊኖርበት እንደሚችልም  ታሪክ ራሱ ምስክር ነው። ድሮ ያወገዝነው አሁን የምንቀበለው ብዙ ነገር አለ። እነ ጋሊሎን መናፍቅ በሚል ያስወገዘውን የመሬት ክብነት እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል። ከሐይማኖቶቻችን የቀዳናቸው አንዳንድ ቀደምት ባህሎቻችንሳ? ዛሬ ላይ እናፍርባቸው የለምን? ሰልጥናለች ህግጋቶቿም የአይሁድ እና የክርስትና አሻራ አለባቸው ተብላ በምትታሰበው ኢንጊሊዝ ውስጥ እንኳን ባልና ሚስት አንድ ናቸው በሚል ሰበብ በህግ ፊት ሴቷ የራሷ ስብእና እንዳይኖራት ለዘመናት ተደርጎ እንደነበረም አንዘነጋም። እሰክ 1891 ድረስም የትዳር አጋራችንን፣ ሚስታችንን፣ በተመጠነ መልኩ መደብደብም የወንዱ መብት ተደርጎ በዚህች አገር ይወሰድ ነበር። 2

ፍጹሙ የምንለው ኃይማኖታችን ስለምን ዛሬ ላይ ደርሰንበታል ብለን ከምናስበው እውነት እና ፍትህ ጋር ትላንት ላይ ተጣላ? መልሱ ግልጽ ነው። ሐይማኖት የቱንም ያክል ከአምላክ በተገኘ መገለጥ ላይ ተመሥርቷል ቢባልም የሚተገበረው እና የሚቀመረው ፍጹም ባልሆነው ሰው እጅ ስለሆነ ስንረዳውም ሆነ ስንተገብረው ከፍጽምና ስለሚጎድል ነው። ሐይማኖትን የምናምነው እኛ ሰዎች እሰከሆንን ድረሰ ደግሞ ሁሉም ሐይማኖቶች የሚያስተምሩት የሰው ኃጢያተኛነት የራሱን አሻራ በሐይማኖታችን ላይ እንዲያጠላ ያደርገዋል። ለዚህም አይደለምን ቅዱሳት መጽሐፍት “ከእናንተ የተነሳ የእግዚአብሔር ስም ይሰደባል” የሚሉን? በሌላ አነጋገር የሐይማኖቱ ተከታዮቹ ኃጢያተኛ መሆናችን ሐይማኖታችንን ሆነ ሐይማኖተኝነታችንን መቼም ፍጹም እንዳይሆን ያደርገዋል። ይኽም ሐይማኖትን በዕለት ተዕለት ኑሮዋችን ውስጥ ተገምጋሚ እኛ ተተቺ ያደርገዋል፤ በመተቸቱም እንበለጽጋለን እንጂ አንከስርም።

እናድምጥ

የእኛን የአማኞቹን ፍጹም አለመሆን የምናውቅ ሁሉ ደግሞ ሐይማኖታችን ሲገመገም እና ሲተች ከመከላከል ከመጀመር ይልቅ በማድመጥ ብንጀምር ብዙ የምናተርፍ ይመስለኛል። ስግብግብ ፓለቲከኞችን ተችተን ስግብግብ ሰባኪዎች ያሉን እኛ ሰባኪዎቻችን አይተቹ የምንልበትንም የሞራል ልዕልናንስ ቢሆን ከየት እናገኘዋለን? የሚተቸንን ሁሉም የሚጠላን አድርገን ማቅረብም ቢሆን እኛን አይጠቅመንም፤ ከአምላክ ተሰደበ ይልቅ አምላክን አሰደብነው ቅኝታችን ቢሆንም እኛንም ሆነ ሌሎችን እንጠቅማለን ። በአደባባይ የፈጸምነውን ነገርስ እንዴት ከትችት ልናስመልጠው እንችላለን? ሐይማኖት ቢሆንም፣ በአደባባይ መፈጸሙ በራሱ፣ በሆነ ደረጃ አስተያየት መስጠት የመቻልን መብት ለሌሎች ያጎናጽፋል፤ እኛንም ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን አድማጭም እንድሆንም ይጠብቅብናል።

ለነገሩ የውጭ ሰው አይንካን ካልሆነ በስተቀር ቅዱሳት የምንላቸው መጽሐፍትስ ቢሆን የሐይማኖት መንገዳችንን በመተቸት የተሞሉ አይደሉምን። እንደ ምሳሌ የነቢያት መጽሐፍትን ማንሳት እንችላለን። እናመልክሀለን የምንለው አምላክስ ራሱ አምልኮዋችሁን ጠላሁት ብሎን ያውቅ የለምን? አሁን ላይ ቢሆንም ጣኦቶቻችን፣ ግብዝነታችን እና ተቃርኖዎቻችን ተነቅሰው መውጣት አለባቸው፤ ትችቶቹንም እንደግብረ መልስ ወስደንም ራሳችንንን ማስተካከል አለብን። ልክ እንደማናቸውም ሥልጣኖች ሁሉ ሐይማኖታዊ ስልጣኖች የሚከበሩ ብቻ ሳይሆኑ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሚተቹም መሆናቸውን ብንቀበል እናተርፋለን። ትችቶችን በልበ ሰፊነት በመቀበላችንም ሐይማኖታችን እና ሐይማኖተኛነታችንን እናስጠብቃለን እንጂ አናስጠቃም። ልብ ብንል በሐይማኖተኝነት እና በሐይማኖት ላይ የሚደርሱ ትችቶች እና የእኛም ልከኛ ምላሾች ሐይማኖታችን እብሪተኛ እንዳይሆን ልክ የሚያስገቡን የአምላክ መሣሪያዎች አድርገን ባየናቸው ነበር። ትችቶቹን ተከትሎ የምናሳየው ትህትናችንም ከአሳይሃለሁ ድንፋታችን ይልቅ የብዙዎችን ልብን በማረከ ነበር።

[1] አንዳንድ ወንጌላውያን አማኞች ሐይማኖት የሚለውን ቃል በአሉታዊነት ወሰደውት ራሳቸውን አማኞች እንጂ ሐይማኖተኞች አድርገው የማይቆጥሩ አሉ። ለእኚህ ዐይነት ሰዎች ሐይማኖት የሚለውን እምነት በሚል ልንተካላቸው እንችላለን።

[2] Doggett, Maeve E. Marriage, Wife-Beating, and the Law in Victorian England. Columbia: University of South Carolina Press, 1993.

Share This Story, Choose Your Platform!

Written by : Dr. Tekalign Nega

Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.

Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.

Subscribe To My Page

BE NOTIFIED ABOUT RECENT UPDATES

One Comment

  1. Medi February 21, 2025 at 11:13 pm - Reply

    God bless you! I have learned a lot!

Leave A Comment