
የስሜት መዝገበ ቃላት
በ ዶ/ር ተካልኝ ነጋ (PhD)
እኔ እና ሀኒ (የትዳር አጋሬ) በሕይወታችን ውስጥ ሆነ ብለን መኮትኮት የምንፈልጋቸው በርካታ በጎ ነገሮች አሉን። ከነዚህ አንዱ አንዳችን ለሌላችን ስሜቶቻችንን መግለጽ መቻል ነው። አንድ ምሽት፣ የተለመደው የቀኑ ውክቢያ ሲጠናቀቅ እና ልጆቻችን ሲያሽልቡ፣ ዛሬ የተሰሙንን ስሜቶች ያለ አንዳች ማብራሪያ ስማቸውን ብቻ እንጥራ አልኳት፤ ሳታቅማማ ተስማማች። ለጥቂት ደቂቃዎች በዐይነ ህሊናችን ቀናችንን ቃኘነው፤ ያስተናገድናቸውን ስሜቶቻችንንም መዘርዘር ጀመርን። ስንጨርስም አግራሞት በተሞላበት መልኩ “ለካ ስሜቶቼን በደንብ መዘርዘር አልችልም” አለችኝ።
ስሜቷን መግለጽ የሚያቅታት ሀኒ ብቻ አይደለችም፤ ችግሩ የብዙዎች ነው። አብዛኞቻችን ስሜቶቻችንን መዘርዘር በሚያስችሉ መዝገበ ቃላት ባለ ጸጎች አይደለንም፤ እንደውም ድሆች ነን ማለትም ይቻላል። እናንተስ ስለራሳችሁ ምን ታስባላችሁ? በስሜት መዝገበ ቃላት ባለጸጎች ናችሁ? ራሳችሁን መመርመር ከፈለጋችሁ ዛሬ ላይ የተሰማኝ ስሜት ብላችሁ ስሜታችሁ ለመዘርዘር ሞክሩ። ቃላቶች ተዥጎደጎዱ ወይስ አጠሯችሁ?
ሰዎች ያስተናገዳችኋቸውን ስሜቶች ዘርዝሩ ሲባሉ የሚመጡላቸው መዝገበ ቃላት ደስ ብሎኛል፣ አዝኛለሁ፣ ተናድኛለሁ ከሚሉት ሦስት ቃላት አለማለፋቸውን ያመለክታሉ። ጥናቶቹ፣ ከባህል ባህል ሊለያይ ቢችልም፣ 87 ስሜትን ለመግለጽ መዋል የሚችሉ ቃላቶች እንዳሉ አሳይተዋል። [1] ራሳችሁን 87 ቃላት ካለው ቋንቋ ውስጥ 3ት ቃላትን ብቻ እንደሚያውቅ ሰው አስቡት። ራሳችሁን የቋንቋው ጥሩ ተናጋር አድርጋችሁ መቁጠር የሚያስችል ድፍረት አላችሁን? አይመስለኝም! በ3 ቃላት ብቻ ስሜትን ለመግለጽ መወሰን በስሜት መዝገበ ቃላት ደካሞች መሆናችንን ያመላክታል።
ችግሩ
የተሰማንን ስሜት ስም መስጠት አለመቻል ጥሩ ነገር አይደለም። ምክንያቱም በቅጡ ያለየናቸውን ስሜቶቻችንን መቆጣጠር እና ለምንፈልገው አላማ መቃኝት አንችልም። በስሜት ገለጻችን ባለጸጋ እንዳንሆን ከዳረጉን ምክንያቶች መካከል ዋንኛውም ስሜቶችን ማስተናገድ፣ በተለይ ደግሞ አሉታዊ የሚባሉትን ስሜቶችን ማስተናገድ፣ ልክ አይደለም ብለን ስለምናስብ ነው። ገና ከልጅነታችን አሉታዊ ስሜቶች ሁሉ ኃጢያት እና ያለ መብሰል ማሳያዎች አድርገን እንድናያቸው ተደርገን ተኮትኩተናል። አስተዳደጋችን ስሜትን እና ስሜታዊነትን የሚያቃልል ከሆነ ደግሞ ስሜቶቻችን ልናደምጣቸው እና ልንረዳቸው የምንጥራቸው ነገሮች ሳይሆኑ ችላ የምንላቸው ይሆናሉ።
ልጅነታችን እና አከባቢያችን ምን አስተማረን? ክስተቶችን ስንተረጉም ስሜቶቻችን የሚጫወቱንን አዎንታዊ ሚና አላናናቀብንም? የተሰማንን ስሜት እንዳናምን ዝም ብለህ ነው፣ ዝም ብለሽ ነው ተብለን አልተብጠለጠልንም? ስሜታችንን በማሳየታችን ብቻ የተቀጣንባቸው ጊዜያትስ የሉምን? አስተዳደጋችን ስሜታችን እንዳልተገባ እየቆጠረው ሳለ ስሜታችንን ለመረዳት ከራሳችን ጋር ጊዜ እንወስዳለን ወይም ለስሜታችን ስም ለመስጠት እንጥራለን ብሎ መጠበቅም ተገቢ አይሆንም። ይኽም የሚሰሙንን ስሜቶች በስማቸው መጥራት እንዳንችል አድርጎናል።
ለምን?
ስሜትን ግን ለምን በክፉ ዐይን ተመለከትነው? ሁለት ምክንያቶችን እናንሳ። አንደኛው ስሜት ቅጽበታዊነት ስላለበት እና ተለዋዋጭ ስለሆነ ነው። እኛ ሰዎች ደግሞ በፍጥነት ከሚቀያየር ነገር ይልቅ ያለ ለውጥ አብሮን የሚዘልቅ ነገር ይስበናል። ሁለተኛው፣ ስሜትን ያልሠለጠነው የሰው ማንነት ወይም የኋላ ቀርነት መገለጫ አድርገን ስለምናየው ነው፤ ስሜትን የግብተኝነት መገለጫ የቀውስ እና የነውጥ ምልክት አድርገን መቅረጻችንም ለዘመነኛው ሰው የማይመጥን ባህርይ አድርገን ስሜትን እንድንመለከተው ያደርገናል።
እውነታው አለመብሰለስ ስሜቶቻችንን በትክክል መግለጽ አለመቻል ነው። ስሜቶቻችንን መግለጽ ብንችል ስሜቶቻንን ምቾት የማይሰጡን ነገሮች መሆናቸው ያበቃል። ስለማፍርባቸውም ልንደብቃቸው አንጣጣርም። ስንበስል፣ አሉታዊ የሚባሉ ስሜቶቻችንን ጭምር፣ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት ልክ መኪና ዳሽ ቦርድ ላይ እንደሚበሩ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ምልክቶች በተመለከትናቸው ነበር። [2] የዳሽ ቦርድ መብራታችን ሲበራ የሆነ ነገር እንደተጠቆምን እንደሆነ በማሰብ ነገሩ እንመረምረዋለን እንጂ አንዳች ነገር እንዳልተፈጠረ በማስብ ችላ አንለውም።
ስሜቶቻችን መረዳት እና በተገቢው መንገድ መግለጽ ባልቻልን ቁጥርስ? በራሳችን ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ ባንፈልግም እንኳን መጨከናችን አይቀርም። የራሳችን ስሜት ምቾት የማይሰጠን ከሆነስ እንዴት የስሜት ነውጥ እያስተናገደ ያለን ሌላን ሰው በትክክል እንረዳለን ደግሞም እናግዛለን ብለንስ ማስብ እንችላለን? ስሜቶቻቸውን የዘነጋንባቸው ሰዎችስ እንዴት አድርገው እንደተረዳናቸው ያስባሉ? ይህም ለራሳችን እንግዳ እንዳንሆን፣ ራሳችንን ሆነ ሌሎችን በተገቢው መልኩ እንድንከባከብ ስሜታችንን በተገቢው ሁኔታ መግለጽ በሚያስችሉን መዝገበ ቃላት ማደርጀት እንዳለብን ያመላክተናል።
ስሜታችንን መቀበል የምንቸገርበት ምክንያት አንዳንዴ ስሜቶቻችን ህመም ስለሚያስከትሉም ነው። ስሜቶቻችን ላይ ማተኮር እና ከስሜቶቻችን ጋር ጊዜ ማሳለፍም ህመማችንን ማባዛት ስለሚመስለን ከማሰላሰል ይልቅ እንሸሻቸዋለን። ስሜትን የመረዳት አስፈላጊነት ሲገባን ግን ስሜቶቻችን መረዳት እና መግለጽ መቻል ጠንካርች እና በሳሎች ብቻ ሊፈጽሙት የሚችሉት መሆኑን እንገነዘባለን። ያለ ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬም ልንተገብረው የምንችለው ጉዳይም አይደለም። የዚኽ ሁሉ ጅማሮ ደግሞ ስሜቶቻችንን መግለጽ ከመቻል ይነሳል፤ በስሜቶቻችን ማፈርም እናቆማለን።
ራሳችንን እንፈትሽ
በስሜት መዝገበ ቃላቶቻችን ባለጸጋ መሆን ጠቃሚ ከሆነ ምን አናድርግ? ሆነ ብለን ስሜቶችንን መግለጽ የሚያስችሉንን ቃላት እናሰባስብ። ስሜቶቻችንን መግለጽም እንጀመር። ይህን ለማድረግ እንዲረዳንም የፕሮፌሰር በርኔ ብራውንስን 13 ምድቦች ውስጥ የከፋፈለቻቸውን 83 የስሜት መዝገበ ቃላትን እንደመነሾ መጠቀም እንችላለን። [3] እያንዳንዱ ምድብ ባማካይም 7 ያክል ዝርዝሮች አሉት እንደማለት ነው። እነዚህን ምድቦችን በመጠቀም የቱን ያክል ስሜታችንን በመግለጽ ስሴታማ መሆናችንን ራሳችንን እንመርምር።
አንዳንዴ እርግጠኝነት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ይጠፋናል ወይም ነገሮች ከቁጥጥራችን ወጭ እንደሆኑ ይሰማናል። ይኽንን ስሜታችንን በቃላት መግለጽ እንችላለን? ሌላ ጊዜ ራሳችንን በንፅፅር ስሜት ውስጥ እናገኘዋለን፤ በንፅፅሩ በልጠንም ሆነ ተበልጠን የምንገኝባቸው ጊዜያት አሉ። እኚኽን ጊዜያትስ መግለጽ በሚያስችሉ ቃላት ባለጸጎች ነን?
ሰው ነንና ማናችንም ሁል ጊዜ ነገሮች ሁሌ በፈለግነው እና ባቀድነው መንገድ አይሄዱልንም። ነገሮቻችን ባልፈለግናቸው መንገድ ሲሄዱ የሚሰማንን ስሜት ለመግለጽስ የምንጠቀማቸው ቃላት አሉን? ካሉንስ ስንት ናቸው? ነገሮች ከጠበቅነው ከእኛ እሳቤ እና ጥበቃ ውጭ በበጎውም ሆነ በአሉታዊው መንገድ የተለዩ ሆነው ስናገኛቸውስ የሚሰማንን ስሜትስ መግለጽ እንችላለን?
አንዳንዴ ውስጣችን ይጎዳል፤ ህመም ይሰማናል። ስንጎዳ ጉዳታችንን ለመግለጽ የምንጠቀማቸው ቃላቶች አሉን ወይስ ስሜቶቻችን ውስጣዊ ምጥ ብቻ ይሆናሉ? ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን መልከ ብዙ ግንኙነቶች ውስጥም በርካታ ስሜቶችን እናስተናግዳለን። እነዚህ ለመግለጽ የሚያስችሉን ቃላቶችስ የትኞቹ ናቸው? ሁላችንም ማድረግ አለብን ወይም መሆን አለብን የምንላቸው ነገሮች አሉን። እኚኽን አለመሆን እና አለማድረግ ደግሞ የሆነ ዐይነት የጎዶሎነት ስሜት እንድናስተናግድ ያደርገናል። የጎደሎነቱን ስሜት መግለጽ የሚያስችሉ ቃላቶች አደርጅተናል? ከሌሎች ሰዎች ጋርስ ትሥሥር መፍጠርን ስናስብ የሚሰሙን በጎ ነገሮች እና ፍርሀቶችም አሉን። በጎ ስሜቶቻችንን ሆነ ፍርሀቶቻችንን መግለጽ የሚያስችሉ በቂ ቃላቶች አሉን?
ልባችን አንዳንዴ ክፍት ይለዋል። ይኽንንን ስሜት ለሌሎች ማካፈል ብንፈልግ በቀላሉ የምንመዛቸው ቃላት አሉን? ሌላ ጊዜ ደግሞ ሕይወት በጎ ጎኑ ፍንትው ይልልናል፤ ልባችንም በደስታ ጮቤ ይረግጣሉ። ይኽንን ደስ የሚል ውስጣዊ ስሜት ከሌሎች ጋር መካፈል የሚያስችሉ ቃላት አለን? ሌላ ጊዜ በሰዎች በደል ይደርስብናል። በደላችንን መግለጽ በሚያስችሉ ቃላትስ የቱን ያክል በልጽገናል? ሰው ነንና ራሳችንም መገምገማችንም አይቀርም። ግምገማው ይዞት የሚመጣውን ስሜትስ በደንብ መግለጽ የሚያስችሉ ቃላት አሉን?
ምን እናድርግ?
አለመታደል ሆኖ አንዳንዶቻችን ከላይ የገለጽኳቸው በርካታ ስሜቶች እንዳሉን እንኳ የማናውቅ አለን። ስሜቶቻችንን ያለ አንዳች ችግር በርካታ ቃላት በመጠቀም መግለጽ የምንችል ካለን ግን እሰየው ነው፤ ራሳችንን እንደ ዕድለኛም እንቁጠር። ራሳችንን ሆነ ሌሎችን መረዳትም አይቸግረንም፤ ተገቢውን እንክብካቤ ለራሳችን ሆነ ለሌሎች ማድረግም እንችላለን።
ስሜቶቻችንን በቃላት ለመግለጽ ካቃተንሳ? ገና ያልተሠራ የቤት ሥራ አለን፤ ከስሜታችን ጋር እንደተራራቅንም ማሰብ እንችላለን። ከስሜታችን ጋር መራራቅ ደግሞ ጥሩ አይደለም፤ ከምልዕት ያጎድለና። ስሜታችንን በተገቢው ቃላት መግለጽ ለምንቸግር ያለኝ ግብዣ ሁለት ነው።
የመጀመሪያው ሆነ ብለን ስሜቶቻችንን መግለጽ የሚያስችሉ ቃላትን በማሰባሰብ እናደርጅ ነው። ስሜትን ራሱ ለመልመድ እንደወሰነው እንደ አንድ ቋንቋ እናስበው፤ የስሜት ቃላትን አናሰባስብ፤ ሆነ ብለን እናጥናቸው። ሁለተኛው እነዚህ ቃላቶች በመጠቀምም ጥቂት ደቂቃዎችን በየዕለቱ በመውሰድ ስሜቶቻችንን መግለጽ እንለማመድ። የየዕለቱ ስሜቶቻችንን መግልጽን ራሳችንን ባስለመድን ቁጥር ስሜቶቻችን ከዕይታችን አድማስ እንዳያመልጡ ማድረግ እንችላለን። ስሜታችንን መግለጽ በመቻላችንም የአዕምሮዋዊ ጤና እና ሰላም በተሻለ ማስጠበቅም እንችላለን።
[1] Brené Brown, Atlas of the heart: Mapping meaningful connection and the language of human experience (Random House, 2021).
[2] Lannin, Daniel G., and Yi Du. The Art and Science of Helping: Developing Fundamental Skills in a Multicultural Age (New York: Taylor & Francis, 2025), 88
[3] Brené Brown, Atlas of the heart, 39-389.
Written by : Dr. Tekalign Nega
Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.
Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.


God bless you 🙏
Thank you. It is fabulous ! I am highly benefited from this article .
Wow I realized How I am poor in my Words and understanding to reflect my feelings. And my Heart feelings to express.
I need to work on It.
Thank u Teku. Blessings!