
ደህና ነን?
በዶ/ር ተካልኝ ነጋ
ከራርመን ስንገናኝ “እንዴት ነህ?” “ደህና ነህ?” እንባባላለን። አሁን ጥያቄውን አሻሽለነው “ሁሉ ደህና ነው?” መባባልም ጀምረናል። የተሻሻለው ጥያቄ ለሕይወት መልከ ብዙነት እውቅና ይሰጣልና ከድፍኑ “ደህና ነህ?” ይልቅ እመርጠዋለሁኝ። “የሁሉ ደህና ነው?” ጥያቄን ሌሎችን ብቻ ሳይሆን ራሳችንንም ብንጠይቅ እናተርፋለን።
ደህና መሆናችን ግን በምን ይለካል? አንዳዶቻችን ጤንነት ከህመም መላቀቅ ብቻ ይመስለናል። እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ትርጉም ጤናማነት ደርዘ ብዙ ነው። [1] የሕይወት ገጾቹም አዕምሮዋችንን፣ ስሜታችን፣ አካላችንን፣ ማኅበራዊነታችንን፣ ሥራችንን፣ ፋይናንሳችንን፣ አከባቢያችንን፣ መንፈሳዊነታችንን ያካትታል። ጤንነትን አካላዊ (ቁሳዊው) ብቻ ካደረግነውስ? ከምለዕት እንጎድላለን። የዚህች መጣጥፍ ትኩረቷ መንፈሳዊ ጤንነትን ብቻ ነው።
መንፈሳዊነት እና ሐይማኖተኝነት
እኛ አገር መንፈሳዊነት ከሐይማኖተኝነት ተነጥሎ አይታይም። የዚኽ ምክንያት እኛ ኢትዮጵያዊያን ሐይማኖተኞች ስለሆን እና መንፈሳዊ የሚባለው ነገር ሁሉ ነፍስ ወይም መንፈስ በሚለው ሐይማኖታዊ መነጽር ብቻ ስለምንመለከተው ነው። ስለዚህም ኢአማኒ የሆነ ሰው ሐይማኖትን የማይቀበል ስለሆነ መንፈሳዊ ሊሆን አይችልም ወደማለት እናዘነብላለን። መንፈሳዊ ተብሎ ለመመደብም የእኛ እምነት ቤተ ሰብ ምድብ ውስጥ መካተትን ቅድመ ሁኔታ የምናደርግም ጥቂት አይደለንም።
በሥነ ሰብ፣ በሥነ ልቦናው እና በፍልስፍናው አተያይስ? መንፈሳዊነት ከሐይማኖተኝነት ጋር ብቻ የተቆራኘ ጉዳይ አይደለም። የዚህ ማሳያው ራሳቸውን “መንፈሳዊ ነገር ግን ሐይማኖተኛ ያልሆነ” ብለው የሚገልጹ ቁጥራቸው እየጨመረ መሆኑ ነው። የ2023ቱን የፒው ሪሰርች መረጃ ከአሜሪካውያኑ መካከል መንፈሳዊ ነገር ግን ሐይማኖተኛ አይደለንም የሚሉት ምጣኔያቸው 22 ከመቶ መድረሱን ያመላክታል። ነገሩ ከ4 አንድ እንደማለት ነው።[2]
“መንፈሳዊ ነገር ግን ሐይማኖተኛ” አይደለሁም የሚሉ በመደበኛ ሐይማኖት ውስጥ ያልተካተቱ አማኒያን ብቻ አይደሉም፤ አንዳንዶቹ ኢአማንያን ናቸው። ይኽ ደግሞ መንፈሳዊነት ምን ዐይነት ትርጉም ቢሰጠው ነው አማንያን እና ኢአማንያን በጋራ ይወክለናል እንዲሉ ያደረጋቸው የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል።
አንዳንድ ኢአማንያን እና አማንያን ራሳቸውን በአንድ ስያሜ መንፈሳዊ ሊሉ እንዴት ቻሉ? ሁለቱም ሕይወት ከሚጨበጠው እና በአዕምሮ ስሌት ብቻ ከሚደረስበት የላቀ ትርጉም አላት ብለው ስለሚያምኑ ነው። ይኽም መንፈሳዊነትን በቁሳዊ ነገር ብቻ እርካታ አያገኝም ባይነት ያደርገዋል፤ የሕይወት መንገዱም ከቁሳዊነት ይልቃል፤ የላቀ ትርጉም እና ዓላማ ፍለጋም አለው።
ለኢአማኒ መንፈሳዊያን መንፈሳዊነት ምንድን ነው? በጥቅሉ የሕይወትን ትርጉም በራስ መፈለግ እና በሕይወት መደነቅ ነው። አድናቆቱ እና ፍለጋው ግን የተመሠረተው እንደ ሐይማኖተኞቹ በአምላክ እና በወደፊታዊነት ላይ ሳይሆን በምክንያት እና በአሁን ላይ ብቻ ነው። አተያዩ በተፈጥሮ ግዝፈት መደነቅን፣ በሕይወት ውስብስነት መገረምን፣ በሰው ልጆት እና በትሥሥራቸው ውበት መሳብን፣ እና እውነትን፣ መረዳትን እና እውቀትን መሻትን ያመለክታል።[3]
ሰዎችም በሕይወቴ ምን ላድርግ? ምን ዐይነትስ ሰው ልሁን? በሕይወት ሳላመቻምች መፈጸም ያለብኝ እና ቅድሚያ የምሰጣቸው ተግባራት ምንድን ናቸው? ብለው መጠየቅ ከጀመሩ አማንያን ሆኑ ኢአማንያን የመንፈሳዊነት ጥያቄዎችን እያነሱ ነው። ለዚህም ነው እንግዲህ መንፈሳዊነት በሕይወት ትርጉም እና ዐላማ ማግኘት ነው በሚል በጥቅሉ የሚበየነው። መንፈሳዊነት በሌላ መልኩ ደግሞ የጉዞ አቅጣጫ እንጂ ደርሰናል የሚባልበት ስፍራ አይደለም።
መገለጫዎቹ
መንፈሳዊያን የሕይወት ምልከታቸው ረቂቅነት ይጎላበታል። የሚታያቸው ቁሳዊው እና የላይ የላዩ ብቻ አይደለም፤ ዕይታቸው ሰፊ እና አጥር አልባ ነው። ልባቸው እና አዕምሮዋቸውም ቢሆን በተቃራኒ አቅጣጫ አይጓተቱም። ሕይወትን የሚያሰላስሏት ሆነ የሚኖሯት በፍጹም ግርምት ነው፤ ሁሉ ነገር ይደንቃቸዋል፤ሁሉ ነገር ጥልቅ እና አንዱ ከሌላው ነገር ጋር በህብር የተያያዘ ነው። በእርግጥም መንፈሳዊ ሆኖ በተፈጥሮ ባህርይ አፉን በግርምት የማይከፍት ነገሮች ከመረዳት አልፈውበት በአድናቆት እጁን አፉ ላይ የማይጭን የለም።
መንፈሳዊያን ዝናን፣ ገንዘብን እና ኃያልነት አያሳድዱም። ምርምራቸው፣ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች እና ትዝብቶቻቸው የሚቃኙት በምን ይጠቅመኛል ስሜት አይደለም። ለተፈጥሮ ያላቸው አክብሮት፣ መገረም እና ፍቅር ይለያል፤ የልጅ ዐይነት መመሰጥ ይታይባቸዋል፤ ተቀኝተውለት ልባቸው አይረካም፤ ቅኔ ይዥጎደጎድላቸዋል። ውበትን እና እውነት ይመስጣቸዋል። አማኞቹ መንፈሳውያን ደግሞ ከእውነት እና ከውበት ጀርባ ሁል ጊዜ አምላክ ይታያቸዋል።
ምንፈሳውያን ስሜታቸው ንቁ ነው፤ ለስሜት ሕይወታቸውም እንግዳ አይደሉም፤ አደማመጣቸው ጥልቅ ነው። እነርሱ የሚታያቸው ለሌሎቻችን አይታየንም፤ የሚሸታቸውን ልብ አንልም፤ የእነርሱን ያክልም ሕይወታችን እርካታን አትሞላም። ተራ እና ተደጋጋሚ የሚባሉ ነገሮችን ሁሉ በፍቅር እና በጥልቅ ትርጉም ይፈጽሟቸዋል፤ የእነርሱን ያክል የምንበላውም አይጣፍጠንምም።
መንፈሳውያን ለጥሩነት ወይም ለባህርይ ግንባታ የሚሰጡት ቦታ እና ዋጋ ትልቅ ነው። የሕይወት ምርጫቸው የተቀዳው ይህንን ባላደርግ ወየውልኝ በሚል የፍርድ ፍርሀት ወይም በምን ይሉኛል ሳይሆን ከፍቅር ነው፤ ከፍቅር ውጭ የሚያደርጉት ነገር የላቸውም። ስለዚህም ከማንም ጋር ያላቸው ግንኙነት በተቀበል ስጥ ስሌት ላይ አይመሠረትም። ሁሉ በፊታቸው የተከበረ ስለሆነ በአክብሮት ይስተናገዳል። የሁሉ ወዳጅ መሆን ይችላሉ፤ ልዩነቶችን አክብረው እና አቻችለው ሳያመቻምቹ ይኖራሉ። የሰው ጠላት የላቸው፤ ትህትና ገንዘባቸው ነው።
መንፈሳውያን ትኩረታቸው ሌሎች ስለሆኑ ለሌሎች ህመም እና ደስታ ቦታ አላቸው፤ አብረው ይስቃሉ፤ አብረው ይከፋሉ። ለግንኙነቶቻቸው ጥንቁቅ እና የሚሳሱ ስለሆኑም ሀሳባቸው ሆነ ድርጊታቸው በሌላ ሰው ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ነገር ሳያስቡት አይናገሩም አይፈጽሙም። መንፈሳውያን መደሰት ያውቃሉ፤ የሕይወትን ውበት ያጣጥማሉ። እኛ እዚህ ግባ በማንላቸውን ጥቂት እና የተለመዱ ነገሮች ይገረሙባቸዋል፤ በየጠዋቱ ጸሀይ መውጧቷ ሁሌ ይገርማቸዋል።
መንፈሳውያን ለዕሴቶቻቸው እሰከ ሞት ድረስ ጨካኞች ናቸው፤ ሕይወታቸው ርካሽ አይደለም። እውነት የሚያስከፍላቸውን ዋጋ እና የሚያመጣባቸውን መከራ አይሸሹትም፤ እንደውም በደስታ ይጋፈጡታል፤ በሞት ላይ መሳቅ እና መሳለቅ ይችላሉ። በሕይወታቸው መሆን አለበት የሚሉት ነገር አላቸው፤ ለዛም ይሠራሉ፤ ለዛም ይኖራሉ።
መንፈሳውያን ራሳቸው አጋነው አያዩም፤ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ልከኛ ነው፤ ተሰባሪነታቸውን እና ተደጋፊነታቸውን ላፍታም አይዘነጉም። እሳሳታለው ስለሚሉ ሲተቹ ያደምጣሉ፤ ለጥፋታቸው ይቅርታን ይጠይቃሉ እንጂ ለለመቀበል ምክንያት አይደረድሩም። ድካማቸውን መመልከትም ሆነ ማመን አይቸግራቸውም። ሕይወትን ሳያቃልሉ አቅልለው ይኖሩታል። የሚፈልጉት ከአብዛኛው ሰው ይለያል እንጂ ብዙ አይደለም። ኑሮዋቸውም ከውስጥ ወደ ውጭ እንጂ ከውጭ በሚመጣ ግፊት ተወዛዋዥ አይደለም። ግርግር መካከል ርግት ያሉ ናቸው።
መንፈሳውያን ከምንም በላይ ተቆራሽ ናቸው። ለጋስ ስለሆኑ ቸርነት የቅጽል ስማቸው ነው፤ በጎ ማድረግ አይቸግራቸውም፤ በጎ ያደረጉለትን እንደ ባለዕዳ አያዩትም። ቸር ሰለሆኑም ለሰዎች ከተገባቸው በላይ መትረው ይሰጣሉ፤ አንዳንዴ ከጉድለትም ጭምር ቆርሶ ማካፈል አይከብዳቸውም። ምሕረት ወዳጃቸው ናት፤ አጥፊ ቢስተካከል በሚል ይወቅሱታል እንጂ በተንኮል አያደቡበትም፤ ውድቀቱንም አይጠብቁም፤ መቼም ቢሆን ሰውን የጥፋቱን ያክል አይቀጡትም።
ትሩፋቱ እና መንገዱ
መንፈሳዊነት ትሩፋቱ ብዙ ነው። ለአሁኑ ለጤናችን የሚሰጠውን ፋይዳ ብቻ እናንሳ። ጥናቶች የመንፈሳውያን አማካይ ዕድሜ ከሌሎች ይልቅ እንደሚረዝም ያሳያሉ። በሕይወት መንገዳቸው በሽታ ፈተና ሲገጥማቸው፣ ሲታመሙ እና አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሲያልፉ አይበገሬ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ከህመም እና ከቀዶ ጥገና በኋላም በቶሎ የማገገም አቅማቸው ይልቃል።[4] እኚህና ያልዘረዘርናቸው በርካታ ሌሎች ትሩፋቶቹ የመንፈሳዊ ደህንነታችን እንዴት እናረጋግጥ የሚለውን ጥያቄ ተገቢ ያደርገዋል።
መንፈሳዊ ጤናችን እንዴት እናረጋግጥ? ከሁሉ በፊት ለእኛ መንፈሳዊነት ምን ማለት እንደሆነ እንገንዘብ። የመንፈሳዊነት ግንዛቤያችን ከሐይማኖታዊ ትውፊት እና ተግባራት ጋር፣ ለአምላክ መኖር እውቅና ከመስጠት ጋር፣ በወርቃማው ሕግ ተገዝቶ መኖር ከመቻል ጋር፣ የመለኮትን መገኘት እውቅና መስጠት እና መገኘቱን ከመለማመድ ጋር፣ የሕይወትን ረቂቅነት በመገንዘብ ከመኖር ጋር፣ ከሌሎች ሰዎች እና ከተፈጥሮ ጋር ጥልቅ ትሥሥርን ከመፍጥር ጋር፣ ፍርሀት የተሞላበትን አክብሮት እና መደነቅን ከእኛ ለሚበልጥ ማንነት ከመስጠት፣ እና እያንዳንዱን ሰው እንደ ቅዱስ እና የተለየ ሰው አድርጎ ከመመልከት ጋር ሊያያዝ ይችላል። [5]ለግንዛቤያችንም ታማኝ ሆነን ለመኖር እንጣር።
ማነኝ? ዓላማዬስ ምንድነው? ዋጋ የምሰጣቸው ነገሮችስ? ብለንም እንጠይቅ። እነዚህ ያቄዎች በባህርያቸው ጤናማ ንጠላን እና የጥሞና ጊዜ ይፈልጋሉ። መነጠሉ እና አሰላስሎው ዘመናዊው ዓለም ውጥረት እና ጥድፊያ የተሞላ ስለሆነ የውጩ ውክቢያ እና ግርግር ውስጣችንን እንዳናደምጥ፣ አስተውሎታችንን እንዳይሰርቅ የምናደርገው ጥረት ነው። ለአሰላስሎ ጊዜ ስንሰጥ ግን መሠረታዊ ጥያቄዎችን ማንሳት የምንችልበት አቅም ይኖረናል። ከሁሉ አብልጠን ዋጋ የምንሰጣቸውን ዕሴቶቻችንንም እናውቃቸዋለን።
ከአሰላስሎው ባሻገር ፅሎት፣ መዝሙር፣ ሙዚቃ፣ የቅዱሳት መጽሐፍት ንባብ፣ ከበራዎች፣ ተፈጥሮ፣ አርት፣ በመንፈሳዊ ሕይወት ለመመንደግ እንደሚረዱን በመገንዘብ የሕይወታችን አካል እናድርጋቸው። መንፈሳዊነት ተራ እና እዚህ ግባ የማይባሉ የዕለት ተዕለት ተግባሮቻችንን በአስተውሎት እና በአሰላስሎ በማድረግ የምናጎለብተው መሆኑን አንዘንጋ። ያኔም በእያንዳንዱ ሰከንድ ውስጥ እንካችሁ የተባልነውን ጸጋ እና የከበበንን ውበት መመልከት የምንችልበት አቅም ይኖረናል፤ ብቻችንም እንደሆንም አይሰማንም፤ መንፈሳዊ ጤናም ይኖረናል፤ ሕይወታችንም ምልዐት ያገኛል።
[1] Chirico, Francesco. “Spiritual well-being in the 21st century: It’s time to review the current WHO’s health definition.” Journal of Health and Social Sciences 1, no. 1 (2016): 11-16.
[2] https://www.pewresearch.org/religion/2023/12/07/who-are-spiritual-but-not-religious-americans/
[3] Taira, T. (2012). Atheist spirituality: a follow on from New Atheism?. Scripta Instituti Donneriani Aboensis, 24, 388–404. https://doi.org/10.30674/scripta.67423.
[4] Puchalski, Christina M. “The role of spirituality in health care.” In Baylor University Medical Center Proceedings, vol. 14, no. 4, pp. 352-357. Taylor & Francis, 2001.
[5] Ammerman, Nancy T. “Spiritual but not religious? Beyond binary choices in the study of religion.” Journal for the scientific study of religion 52, no. 2 (2013): 258-278.
Written by : Dr. Tekalign Nega
Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.
Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.


So deep and makes to pause and think. Found it very much helpful. Thank u dear!
So deep and makes to pause and think. Found it very much helpful . Thank u dear!
It’s a good read indeed. I wish to read the other aspect of health such as mental, social, finanacial, environmental and the like in your future articles.
Thank you for your intellectual contribution.
Much grace!
Hi Teka,
How do I get an English translation of the articles?
Fr. Tanui.
It is a nice article, I learned a lot! God bless you more!
በጣም መንፈሳዊ በሽታ ውስጥ እንዳልሁ ነግሮኝል:: ግን ግን ይሄን መንፈሳዊነት ከመንፈሳዊ አለም ጋር ያለው ትይይዝ እንዴት ይታያል? ይሄን መንፈሳዊን እዚህ በ እኛው በእኛው ንግግርና ጥልቅ አሰላስሎ የምንጋግረው ወይስ ከመንፈሳዊ አለም አለም ጋር ባለውን ተራክቦ የሚወልድ?
Dear Father Martin, thank you for your interest to get the English version. Kindly find it in this link ( https://tekalignnega.com/2025/01/11/are-we-well/ ) .