ነርቬን ነካው!

በዶ/ር ተካልኝ ነጋ አንጎሬ

አንዳንድ ነገሮች ሁሌም ይገርሙኛል፤ በተለይም ለአንድ ዓይነት ክስተት የምንሰጠው ተቃራኒ ትርጉም ይደንቀኛል። ነገሩን ለማስረዳት አንድ ተግባራዊ ምሳሌ ላንሳ። በማኅበራዊ ሚዲያ ዓለም “ብሎክ አደረግሁት” ወይም “ብሎክ አደረገኝ” የሚሉ ንግግሮችን ደጋግመን እንሰማለን። ብሎክ ማድረግና መደረግ የተለያዩ ተግባራት ቢሆኑም፣ ክስተቱን የምንተረጉምበት መንገድ ግን በሚገርም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው።

ብሎክ አድራጊው “አባረርኩት” በሚል ኩራት ነገሩን ይገልጸዋል። አሁን ላይማ “በብሎክ አሰናብትሃለሁ” የሚለው ዛቻ፣ የአሸናፊነት መገለጫ ተደርጎ መወሰድ ጀምሯል። መልዕክቱ ግልጽ ነው፦ “ለአንተ አልገኝም፤ ብትፈልገኝም አታገኘኝም፤ ከእንግዲህ የእኔ ጉዳይ አያገባህም” የሚል የግንኙነት መቋጫ።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ብሎክ የተደረገው ሰው ይህንኑ ክስተት ለራሱ ክብር ማሳያ አድርጎ ያቀርበዋል። መታገዱን የብሎክ አድራጊው “አቅመ-ቢስነት” እና “ትዕግሥት ማጣት” ማረጋገጫ አድርጎ ይቆጥረዋል። ሌላ ቦታ ላይ ስለ ብሎክ አድራጊው አሉታዊ ነገር ሲነሳም፣ ነገሩን ከፈረሱ አፍ ሳይሰማ “እኔም ደርሶብኛል” በሚል በድንጋይ ወገራው ይተባበራል። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን፣ በሁለቱም ወገን ጸጸት፣ መመለስ ወይም ራስን በሌላው መነጽር መመዘን አይታይም። ስሜታችንን እና ሥነ ልቦናችንን የጎዳው ነገርም ማናችንንም ሳያሳደገን፣ በመካከላችን መቃቃርን ብቻ ዘርቶ ያልፋል።

በእርግጥ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የ“ብሎክ” አማራጭ የተቀመጠው በምክንያት ነው። አንዳንዴም ብሎክ ማድረግ በእርግጥም ያስፈልጋል። ይህ አማራጭ ተገቢ ያልሆነ ሥነ-ልቦናዊና የቃል ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎችን ለመከላከል ታስቦ የተዘጋጀ መፍትሄ ነው። በዲጂታሉ መንደር ሰውን ማዋረድና ስሜት መጉዳትን እንደ ዝና የሚቆጥሩ ተሳዳቢዎችና ዛቾች መኖራቸው ሃቅ ነው። ከብሎክ በስተጀርባ ያለው ዋና ፍላጎትም “እፎይታን” መፈለግ ነው፤ የሌላው ሰው ድምፅና መገኘት ሰላማችንን ስለረበሸው፣ ግንኙነታችን እያበለጸገን አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ስንደርስ የምንወስደው እርምጃ ነው። በገጻችን ላይ ሙሉ ቁጥጥር ስላለን፣ ባሻን ጊዜ የማንፈልገውን እናሰናብታለን።

ነገር ግን ዋናው ጥያቄ ያለው እዚህ ላይ ነው፦ በየዕለት ተዕለቱ የገጽ ለገጽ ማኅበራዊው ዓለምስ? እዚህ ጋ ሁሌ ሸሽተን አንችለውም። ነርቫችንን የሚነካው ሰው ሸሽተን የማናመልጠው ወይም ልናባርረው የማንችለው የቅርብ ሰው ከሆነስ? አብሮ መቀጠላችን የግድ በሆነበት ሁኔታ፣ ሌላኛው ሰው ትዕግሥታችንን የሚፈታተን አቀራረብ ካለውና እኛነታችንን ወደማንወደው አቅጣጫ የሚገፋው ከሆነ ምን እናደርጋለን?

ብዙውን ጊዜ ከጥንካሬያችን ይልቅ ድካማችን ጎልቶ ሲወጣ፣ የችግሩን ምንጭ ሌላው ላይ ማድረጉ ይቀልለናል። ሲሰድቡን የተሳደብን ቀን የተሳሳትን አይመስለንም። ተሰድበን አለመሳደብን ምርጫችን ማድረግ የሚያስችል ማንነት መገንባት የእኛ ኃላፊነት እንደሆነም እንዘነጋለን። ጌታችን “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ” (1ኛ ጴጥሮስ 2፡23) የተባለው ለትምህርታችን መሆኑን፣ ስሜታችንና ሥነ ልቦናችን መነካቱ ያስረሳናል።

ለማንወደው እኛነታችን መገለጥ መንስኤው በዋነኛነት የገዛ ድካማችን መሆኑን ስንዘነጋ፣ ዓይናችንን ከማንወደው እኛነታችን ላይ አንስተን ቆስቋሹ ላይ ብቻ እናተኩራለን። ላልወደድነው እኛነታችን ሌላውን መክሰስ የሚሰጠን እረፍት ግን ለጥቂት ጊዜ ነው። ያ በቅጽበት የቀየረን ትንኮሳ አልፎ ጸጥታ ሲሰፍን ጸጸት ይወረናል። “ለምን እንዲህ ዓይነት ምላሽ ሰጠሁ? የቁጣዬ ልክ ተገቢ ነበር?” ብለን እንብሰለሰላለን። ወደ ልባችን ስንመለስ የተናደድንበት ጉዳይ የሚያስቅ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፤ ሆኖም የቁጣው ማዕበል ያደረሰው ምስቅልቅል በቀላሉ የሚስተካከል አይደለም። ይህ የሚያሳየው፣ አሁናዊውን ክስተት በወቅታዊ መነጽር ብቻ ሳይሆን፣ በትላንትናው ያልተፈታ የትውስታ ቅኝት ውስጥ ሆነን እያየነው መሆኑን ነው።

ጸጸት ብቻውን ነገ ላይ ከመውደቅ ዋስትና አይሆንም። በተመሳሳይ ጉዳይ ደጋግመን በቁጣ ስንገለጥ፣ ሰዎች በእኛ ላይ ያላቸው እምነት እየቀነሰና በዙሪያችን የፍርሃት ድባብ እየነገሠ ይመጣል። በቀላሉ የሚያስቆጣን ጉዳይም “ይህንን ጉዳይስ አታንሱበት” በሚል መታወቂያችን ይሆናል። ድካም ሆኖ “አይነሳ” የሚባል ነገር ደግሞ የምናድግበት አቅጣጫ አይሆንም።

ታዲያ ሌሎች ምክንያት ሆነውን በተደጋጋሚ የተመለከትነው ድካማችን የመሻሻያ ዕድል እንዲሆን ምን እናድርግ? መፍትሄው ነርቫችንን የሚነኩትን ስር የሰደዱ ምክንያቶች መመርመርና ከእውነታው ጋር መጋፊጥ ነው። የዚህ ራስ-ፍተሻ ዓላማም በስሜትና በምላሽ እንድንበስል ማገዝ ነው። ያልበሰለ ሰው የትላንት እስረኛ በመሆኑ ክስተቶችን የሚመለከተው በተከላካይና በአጥቂነት መንፈስ ብቻ ነው። ለዚህም ሦስት ቁልፍ የራስ-ፍተሻ ነጥቦችን ልብ ማለት ይገባል፦

በመጀመሪያ፣ ከፍንዳታችን በፊት ምን ቀደመ? የሚለውን እንመርምር። ስናስተውል ድንገቴ የሚመስሉ ነገሮች ሁሉ ድንገቴ አለመሆናቸውን መረዳት አይከብደንም። ድንገቴ የመሰሉን በሌሎች ጉዳዮች ሐሳባችን ስለተያዘ እንጂ አመላካች ምልክቶች ስላልነበሩ አይደለም። የሕይወት ጉዟችንን ፈንጂ የተቀበሩባቸው ምልክቶች እንዳሉበት ሜዳ አድርገን ከተመለከትነው፣ የፈንጂዎቹን ምልክት ለይቶ ማወቅ ላለመርገጥና ላለመፈንዳት ይረዳል።

ሁለተኛ፣ ክስተቱ ምን ዓይነት ትውስታን በውስጣችን ሕያው አደረገው? የሚለውን እንጠይቅ። ምናልባት “አመሰግናለሁ” አለመባል ያስቆጣን የአሁኑ ክስተት ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም ለሠራናቸው ሥራዎች እውቅና ማጣታችን የፈጠረብን የቆየ የልብ ስብራት ሊሆን ይችላል። በሌላ አነጋገር፣ ድንገቴው ምላሻችን አብሮን የከረመን ነገር ግን ያልተጋፈጥነውን ምክንያት እያመላከተን ሊሆን ይችላል። ይህንን ምክንያት መቋጫ ካላበጀንለት፣ ደጋግመን በአንድ ዓይነት ክስተት ወደማንፈልገው አቅጣጫ ልንቆሰቆስ እንችላለን። ክስተቱን ግን ራሳችንን ለመረዳት ከተጠቀምንበት፣ ተመሳሳይ ነገር ወደማንፈልገው አቅጣጫ እንዳይመራን ገደብ ማድረግ እንችላለን።

ሦሥተኛ፣ ሰውነታችን የሚሰጠንን አካላዊ ምልክቶች እናድምጥ። ከመቆጣታችን በፊት እንደ አንገት መወጠር፣ ፊት መቅላት ወይም ሆድ መቁረጥ ያሉ ምልክቶች ይታያሉ። እነዚህን ማስተዋል “እየጋልኩ ነው” የሚል ንቃት ይፈጥራል። በሐሳባችን ላይ ቀድመን ከነቃን ደግሞ በምላሻችን ላይም መንቃት እንችላለን። ሐሳባችን ስሜታችንን መግራት ካቃተው ደግሞ፣ ሐሳባችንን በሌላ ሐሳብ ለማስቆም በመሞከር ብቻ አናብቃ፤ ይልቁንም አካላችንን በመጠቀም (ለምሳሌ ትንፋሽን በጥልቀት በመሳብ) ራሳችንን ለማረጋጋት እንጠቀም።

ባጠቃላይ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ሰውን በ“ብሎክ” ማሰናበት ቀላል እንደሆነው ሁሉ፣ በእውነተኛው ሕይወት ግን ነርቫችንን የሚነኩብንን ሰዎችና ምክንያቶች በምርመራና በብስለት ማስተናገድ ይኖርብናል። መፍትሔው ችግሩን በብሎክ ከመሸሽ ይልቅ፣ ከውጫዊ ወቀሳና ከትላንት ትውስታ እስረኝነት ወጥተን ለራሳችን ንቁ ጠባቂ መሆን ነው። በአካላዊ ማስጠንቀቂያዎች ላይ በመንቃትና በረጋ ትንፋሽ ስሜታችንን በመግራት፣ ግንኙነታችንን ከአጥቂነት ወደ መማር መንፈስ መለወጥ እንችላለን። ይህ ሲሆን ጸጸትን ወደ ብስለት፣ ፍንዳታን ደግሞ ወደ መረጋጋት በመቀየር፣ በማኅበራዊው መስተጋብራችን ውስጥ በብሎክ ኩራት ሳይሆን በትክክለኛ ማንነት የምንቆም የተሻለ ሰብእና ያላቸው ሰዎች እንሆናለን።

Share This Story, Choose Your Platform!

Written by : Dr. Tekalign Nega

Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.

Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.

Subscribe To My Page

BE NOTIFIED ABOUT RECENT UPDATES

Leave A Comment