
ምክር ለሰባኪያን
በዶ/ር ተካልኝ ነጋ አንጎሬ
የእምነታችን መሰረት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ለቅዱሳት መጻህፍት ያለን ጥልቅ አክብሮት እና መታዘዝ ነው። ቅዱሳት መጻሕፍት ሲሰበኩም “እግዚአብሔር አንድ ነገር ይናገረኛል” በሚል ልብና ስሜት እናዳምጣለን። ቅዱሳት መጻሕፍቱም ሰምተናቸው ባንተገብራቸው እንደማናተርፍ ይነግሩናል (ያዕቆብ 1:22-25)። ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው ቅዱሳት መጻሕፍትን እየጠቀስን መልእክት በምናቀርበው በእኛ በሰባኪዎቹ ላይ ነው። ግቤ መደመጣችን እና የቅዱሳት መጻሕፍት ባህሪያቸው ለእኛ ለሰባኪዎቹ ምን አይነት መልእክት እንደሚያስተላልፍ መፈተሽ ነው።
የሰባኪ ልብ
እንደ አምላክ መልእክተኞች መደመጥ ምን አይነት ስሜት ይፈጥራል (ገላ 4፡14)? ያኩራራል? ያስታብያል? ያመኑንን ለራሳችን መጠቀሚያ እንድናደርጋቸው ያበረታታል? በፍጹም! በአማኞች ዘንድ ቅዱሳት መጻሕፍት የአምላክ ድምፆች ናቸው የሚለው እምነት በሰባኪዎች ዘንድ ተጨማሪ የኃላፊነት ሸክምን መፍጠር አለበት። መሰማት፣ በተለይም እንደ አምላክ ድምጽ መሰማት፣ ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን መረዳት አለብን። የሌሎችን ሕይወት የሚቃኝ ንግግር ለመናገር ያገኘነውን ዕድል በአክብሮትና በጥንቃቄ መቅረብ ያስፈልገናል። የጥንቃቄያችን አንዱ መገለጫ ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን አሳስተን እና ለራሳችን ጥቅም አመቻችተን እንዳንጠቅስ መጣር ነው።
የስብከታችን ግብ በጎቹን የመመገብ፣ የመንከባከብና የመጠበቅ አገልግሎት መሆኑን ራሳችንን ሁሌ ማስታወስም ይገባናል። ይህንን ካስታወስን፣ እንዳመጣልንና እንደተሰማን ቶሎ አንናገርም። የእግዚአብሔርን ቃል ስንሰብክ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ የአጻጻፍ ዘውግ መቅረቡንም እናስተውላለን። ወንጌላትን የምንረዳበት መንገድና የጥበብ መጻሕፍትን የምንረዳበት መንገድ በምንም አይነት አንድ አለመሆኑን አለመገንዘብ ግን መልእክታቸውን እንድንስት ያደርገናል። መውቀስ የሌለብንን ተቻኩለን ስንወቅስ፣ ማወደስ የሌለብንንም ስናሞግስ እንገኛለን።
ምሳሌን እንደ ምሳሌ
የቅዱሳት መጻሕፍት የአጻጻፍ ዘውግ እንዴት ትምህርታችንን ሊቃኘው እንደሚገባ ለማሳየትም የጥበብ መጽሐፍ በሚል ከሚበየኑት መካከል አንዱ የሆነውን መጽሐፈ ምሳሌን በማንሳት እንመልከት። በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ የምናገኛቸው ሃያ ምዕራፎች (ከ10-29) ባህሪያቸው ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን፣ በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ከምናገኛቸው ሌሎች ምዕራፎችም ይለያሉ። እነዚህ ምዕራፎች (ከ10-29) አባት ልጁን በጥበብ መንገድ እንዲሄድና ከሞኝነት መንገድ እንዲጠበቅ ከሚመክርበት ከመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ምዕራፎች (ከ1-9) ሆነ ከማጠቃለያዎቹ (30-31) ይለያሉ።
ሃያዎቹ ምዕራፎች የሰለሞን ጥበቦች በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ ምክሮች በሰለሞን ስም ምንም ቢነገሩም፣ ከሰለሞን ዘመን የቀደሙ ስለሆኑ ቀደምት ጥበቦች በመባል ይታወቃሉ። ምክሮቹም ማብራሪያ ያልታከለባቸው አጫጭር ናቸው። በጥንቃቄ ካላነበብናቸውም ብዙ ስህተቶችን ልንሠራ እንችላለን። ይህ እንዳይሆን ከባህሪያቸው የተወሰኑትን እናንሳ። እነዚህን ምንባባት የእግዚአብሔርን ሙሉ ምክር ታሳቢ ሳያደርጉ በተናጥል እንደ ህግ እና እንደተስፋ መስበክም ለብዙ ስህተት ይዳርጋል።
በሃያዎቹ ምዕራፎች ውስጥ የምናገኛቸው አንዳንድ ምክሮቹ ገለጻዎች ብቻ ናቸው፤ የገለጹትን ነገር ሁሉ ትክክል ነው ብለው አጽድቀውታል ማለት ግን አይደለም። ይህም ሕይወታችንን በብቸኝነት እንድንረዳበት የተሰጡ መርሆች እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። በደንብ ከተመለከትናቸው የሚነግሩን የማኅበረሰቡን ቅኝት እንጂ የነገሩን ልክነት ሆነ ስህተትነት አይደለም። ለምሳሌ ምሳሌ 14:20ን እንውሰድ። ክፍሉ “ድሆችን ወዳጆቻቸው እንኳ ይጠሏቸዋል፤ ባለጠጎች ግን ብዙ ወዳጆች አሏቸው” ይላል። ከዚህ ክፍል በመነሳት የሀብታም ወዳጅ እና የድሆች ጠላት እንሁን? በፍጹም! ይህንን ክፍል አንብበን የመወደድን መለኮታዊ ሚስጥር ሀብታም መሆን ነው ካልን በእርግጥም እንስታለን፤ ድህነትን እና ሀብትንም የአምላክ መታጣት እና አብሮነት መገለጫም ይመስለናል።
ምሳሌ 14፡20 የነገረን ሰዎች፣ ኢኮኖሚያዊ ደረጃን እየተመለከቱ፣ አንዳቸው ሌላቸውን እንዴት እንደሚመለከቱ ነው። አምላካዊው ጥበብስ? ከማኅበራዊው አተያይ እጅጉን ይለያል። “ሰው የድኾችን ጩኸት ላለመስማት ጆሮውን ቢዘጋ፣ እርሱም ይጮኻል፤ መልስም አያገኝም።” (ምሳሌ 21፡13) ይላል። “ለድኻ የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ ስላደረገውም ተግባር ዋጋ ይከፍለዋል።” (ምሳሌ 19፡17) ብሎም ይመክራል። ከእነዚህ ምንባባት ከድሆች ጋር ያለን የግንኙነት አይነት ከአምላክ ጋር ያለውን ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን እንረዳለን። ድሆችን ንቆ በአምላክ ዘንድ መከበር የሚባል ነገርን በፍጹም ልናስበው የማይገባ መሆኑንም እናውቃለን።
ክፍሉ ማኅበራዊ ገለጻ መሆኑን እንዴት አወቅን? አምላክ ይላል ተብሎ በቀጥታ ባለመጻፉ ብቻ አይደለም። ከሌሎች ቀጥተኛ የአምላክ ትእዛዛት እና መርሆች ጭምር ጋር አስተያይተነውም ነው። ከሌሎች ምንባባት ተነስተን ሰውን ከገንዘቡ የተነሳ መውደድ ሆነ መጥላት በአምላክ ፊት ጽዩፍ እንደሆነ እናውቃለን። ለዚህም ነው በብሉይም ቢሆን በሀብት ሚዛን የሚደረግ ማበላለጥ ልክ እንዳልሆነ የተነገረው (ዘሌዋውያን 19:15፣ ዘጸአት 23:3፣ ዘዳግም 1:17). ለዚህም ነው የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሀብትን እያየች በማድላቷ ስትወቀስ የምናገኛት (1ኛ ቆሮንቶስ 11:17-22)። ስለዚህም ምንባቡ የመወደድና የመጠላት መለኮታዊ ምሥጢሮች በሚል በሚያቋምጥ ርእስ ታጅቦ ለምዕመናን መቼም መቅረቡ ትክክል አይሆንም።
በሃያዎቹ ምዕራፎች ውስጥ እንደ መርህና እንደ መመሪያ የቀረቡት አንዳንድ ንግግሮችም እንዲሁ ጥበብ የተሞላ ንግግር እንጂ የነገረ ጉዳዩን ሁለንተናዊ ገጽታ የሚያሳዩ አለመሆናቸውን መገንዘብ ይገባል። የዚህ ሁነኛው ማሳያ በንጽጽር ካየናቸው ተቃራኒ ሊባሉ የሚችሉ መርሆቹን በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ተካተው ማግኘታችን ነው። እንደ ማሳያም ምሳሌ 6:6-11ን እና ምሳሌ 15:16ን በንጽጽር መመልከት እንችላለን። ምሳሌ 6:6-11ን ለብቻ ስናነብ ድህነትን ከስንፍናና ጥበብ ከማጣት ጋር አያይዞት እናገኛለን። ከዚህ ምንባብ ተነስተን እያንዳንዱን ድህነት ግን የስንፍናና የጥበብ ማጣት ውጤት ነው ልንል እንችላለን? ድሃ መሆን በአምላክ ፊት የሚያስወቅስ ነው ብለን ልንፈርጅ እንችላለን? ባለጠግነትንም እንዲሁ የታታሪነትና የጠቢብነት ምልክት አድርገን ማየት እንችላለን? ድሃስ ተወቃሽ፣ ሀብታምስ ተወዳሽ ሊሆን ነውን? በፍጹም! እንዲህ ከፈረድን ሆነ ካመንን እጅጉን ተሳስተናል፤ ሚዛንም ስተናል። ከዚህ ምንባብ ልንለው የምንችለው ነገር አንዳንዱ ድህነት ከስንፍና ጋር ሊያያዝ ይችላል ብቻ ነው። ከዚህ አልፈን ድህነትን ሁሉ የስንፍና ውጤት ነው ካልን ግን ተሳስተናል።
ድህነት ሁሉ የስንፍና ውጤት ቢሆን ኖሮ ምሳሌ 15:16 “እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር፣ ሁከት ካለበት ትልቅ ሀብት ይበልጣል” ባላለን ነበር። በዚህ ክፍል ጥቂት ነገር ያላቸው ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ብዙ ካካበቱ ይልቅ የተሻሉ ተደርገው ቀርበዋል። የመጽሐፉን ሙሉ ምክር ከሰማንም የማኅበራዊ ፍትህ መታጣት የአብዛኛው ድህነታችን መነሾ መሆኑንም እንረዳለን። የዚህ ማሳያው ምሳሌ 13:23 ነው። ይህ ክፍል “የድሆች እርሻ የተትረፈረፈ ምርት ያስገኛል፤ የፍትህ መጓደል ግን ጠራርጎ ይወስደዋል” በማለት አንዳንዱ ድህነት ምንጩ የፍትህ መጓደል መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል። ይህንን እውነትም በየቀኑ መስተጋብራችን ውስጥ ሁል ጊዜ የምናየውም ነው።
እናስ?
ስንሰብክ፣ በተለይ ደግሞ ከጥበብ ዘውጎች አንድ ጥቅስ አንስተን ለነገር ጉዳዩ የመጨረሻ ድምዳሜ ለመስጠት አንቻኮል። ምዕመኑን ለማነሳሳትና ለማነቃቃት ያለን ፍላጎት ሰፊውን እይታችንን እንዳይጋርደውም ሰከን እንበል፤ በስብከታችን ስለሚጎዳው ሰው አምላክ ግድ እንደሚለውም አንዘንጋ። ከሃሳባዊ አስተምህሮቶች ፊታችንን ወደ ዕለት ተዕለታዊ ርዕሶች ማዞራችን የሚያስመሰግነን ቢሆንም፣ እንደ ሀብትና ድህነት፣ እንደ ጋብቻና ልጆች፣ ከወላጆች ጋር ስላሉ ግንኙነቶች ስናስተምር ሰከን እንበል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሕይወት የተሻለ ያስተማረቻቸው እና ተገቢውን ትንታኔ መስጠት የሚችሉ ምሁራን በመካከላችን እንዳሉም አንዘንጋ። ድፍረታችንንም እንደ እውቀት አንውሰድ።
የመስበክ ዕድላችንንም የእኛን ሕይወት ማጽደቂያ መሳሪያ አናድርገው፤ እኛ የስኬት መለኪያዎች አለመሆናችን ከአእምሯችን አይጥፋ። እንደ ሰባኪ የእኛ ግብ ልባችንን የነካውንና ከእኛ ሕይወት ጋር ገጠመ ያልነውን ክፍል ብቻ ከቅዱሳት መጻሕፍት ይዞ ለድምዳሜ መክነፍ መሆን የለበትም። ከሰከነ ሕይወት ካልተወለደ ስብከት እንደገነባው ባላነሰ እንደሚያፈርስ እንገንዘብ።
የጥበብ መጽሐፍ ባህሪ እያንዳንዱ ክፍል አንጻራዊ መሆኑን ተገንዝበን በነገረ ጉዳዩ ላይ ሌላ ምን ተብሏል የሚለውን ለማጣራት ጊዜ እንውሰድ። ምንባቡን ስናጠናም ለምን የሚለውን ጥያቄም እንጠይቅ። ለምን ሀብታም ብዙ ወዳጆች አሉት? የእርሱ ወዳጆችስ በእርግጥ እውነተኛ ወዳጆች ናቸውን የሚለውንም ጥያቄ እናንሳ። አምላክስ ሰዎች እንደሚያዩ ያያልን የሚለውንም እናሰላስል። ይህ እንዲሆን ደግሞ የመረጥነው ክፍል ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ያለው ዝምድናስ ምንድን ነው የሚለውን እንፈትሽ።
በአዲስ ኪዳን እንደሚኖር ሰው ደግሞ በተለየ ሁኔታ የአዲስ ኪዳን ትምህርትስ በጉዳዩ ላይ ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ ሁል ጊዜ እናንሳ። የሁሉ ምሳሌ በሆነ በጌታ ዓይንስ ዓለም ራሷን የገለጸችበት ጥበቡ የቱን ያህል ጥበብ ነው የሚለውን እናሰላስል? የጌታ ሞኝነት ከሰው ጥበብ ይልቅ የጠባባቸው ጊዜያት ብዙ መሆናቸውንም እናስታውስ።
ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ አንስተን፣ በተለይም ብዙዎችን የሚነካ ማኅበራዊ ጉዳይን አንስተን፣ በጉዳዩ ላይ አንድ ጥቅስ ብቻ እንዳለ አስመስለን አንስበክ፤ ሰዎችንም ለማያስፈልግ ኩነኔ ሆነ ውዳሴም አናጣድፍ። እንዲህ አይነት ስብከት ቢያስወቅስ እንጂ አያንጽም። የሚያሳብቀውም የእኛን የግንዛቤ እጥረት ብቻ ይሆናል። ለመስበክ የተሰጠንን ዕድል በብዙ አክብሮትና ፍርሃት እንፈጽም።
Written by : Dr. Tekalign Nega
Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.
Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.


Oh thank you so much May God bless you and your family