ወንድነት
የተከታታይ ሳምንታችን የትምህርታችን መጨረሻ ስለነበር ዘግየት ብለን ነበር የወጣቶችን ፕሮግራም የጨረስነው። ውጩም ጨለምለም ማለት ጀምሯልና ጥቂት አብሬያቸው ሳልጫወት ልጆቼ እንዳይተኙብኝ በሚል ወደ ቤት ለመሄድ ጠደፍ ጠደፍ እኔም ማለቴ አልቀረም። በጥድፊያዬ መሀል “ዶ/ር ላንድ ደቂቃ ላናግርህ እችላለሁ አለኝ?” “ሥራ እና ክርስትና” የሚለውን ትምህርታችንን በንቁ ተሳትፎ ሲከታታል የነበረ ወጣት ድምጽ። ላፍታም ሳላመነታ “በደስታ፣” ብዬ ቆም አልኩኝ። ቀጥሎ የተጠየኩት ነገር ያልጠበኩት ነበር።
ወጣቱ ከትምህርቴ መሀል የተሀድሶው መሪው ማርቲን ሉተር ተናግሮታል ብዬ የጠቀስኩትን መዘዝ አደረገ። ያነሳው ንግግር “አንድ አባት የልጁን የሽንት ጨርቅ ሲያጥብ የሚመለከቱት ሴታ ሴቱ ሞኝ ቢሉትም እግዚአብሔር እና መላዕክቱ ግን በሚያደርገው ነገር በመደሰት ፈገግ ይላሉ።” የሚለውን ነበር። ወጣቱን የተረበሸው ተራ የሚባለውን የዕለት ተዕለት ተግባር ጨምሮ ማንኛውንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር በሚል እስካደረግነው ድረስ አምላክ ይከብርበታል በማለቴ አልነበረም። የረበሸው ማርቲን ሉተር የሴት ልጅ ሚና ብሎ ያሰበውን ነገር ወንዱ እንደፈጸመው አድርጎ ማቅረቡ ነበር፤ አባት የልጁን የሽንት ጨርቅ ማጠቡም ምቾት ነስቶታል።
የተለያየ ሚና?
ወጣቱ ወንድ የሴት ልጅ ተብሎ የሚታወቀውን ሚና መጫወቱ ለምን ረበሸው? ከንግግራችን የገቡኝ ነገሮች ነበሩ። ወጣቱ የወንድ እና ሤት ማኅበራዊ ሚናቸው የተለየ ነው የሚል ትምህርትን በክርስትና ስም አድምጧል፤ የሴትን ሥራ የሚሠራ ሰው ሴታ ሴት ተብሎ በማኅበረሰቡ ንቀት ዐይን ሲታይ ተመልክቷል፣ አንዳንድ ክርስቲያን ሴቶችም “በሴት ሥራ” የሚሳተፍን ወንድ “ወንድ አይመስለኝም” ሲሉም ሰምቷል።
ማኅበረሰባችን ወንድነት እና ሴትነት እያለን ያለው ነገር ምንድን ነው? ወንድነት ቆፍጣናነት ሆኗል፤ ውጭ ውጭ ማለትም መስሏል። ሴትነት ደግሞ ልስላሴ እና እንክብካቤ እና የማጀት ሕይወት ተደርጎ ተስሏል። እንዲህ ዓይነቱ መኅበራዊ አመለካከትም ለስላሴ የሚባሉ ማኅበረዊ ክህሎቶችን የሴቶቹ ብቻ ተደርገዋል። በጓዳ ጎድጓዳው መሳተፍ ለወንድነት ከደረጃ መውረድ ተደርጎም ተበይኗል። ወንድ እንደ ሴቶች ስሜቱን የመግለጽ ተፈጥሮዋዊ መብቱን ተነፍጓል፤ ከገለጠም እንደ ደካማ ይታያል። አመለካከቱም ማኅበረሰባችን ውስጥ ዕድሜ ጠገብ ነው።
ቤት ውስጥ ለወንድ ተፍ ተፍ ማለት እና ስሜትን መግለጽ በእርግጥም ችግር ነውን? ለምንስ ወንዶች ለሴቶች እና ለልጆች ፍላጎት ቦታ እንዳይሰጡና እንዳያግዙዋቸው ሆኑ? ስሜትን ገላልጦ መተንፈስ እና ተንከባባኪነትን ማሳየት እንዴትስ ኃጢያት ሆኖ መቆጣት ግን ለወንድነት ጽድቅ ሆነ? እንዲህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ባልና ሚስት ቀኑን ሙሉ ተመሳሳይ ሥራ ላይ እየዋሉ ሚስቲቱ ሁሌ ቀድማ ከእንቅልፍ ተነሺ እና ዘግይታ ተኚ አድርጓታል። የቤት ውስጥ እገዛ ብትፈልግም እገዛን መጠየቋን መዳፈር እና ችግር አድርጋ እንድትመለከተው ተኮትኩታለች።
ከየት ተማርነው?
ወንድነትን ስሜት አልባነት ያደረገው ግን ማነው? አምላክ፣ ተፈጥሮ ወይስ ማኅበረሰባችን? በሴት እና በወንድ ስሜታዊነት ምላሽ እና አገላለጽ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ምን ያሳያሉ? ከ6 ወር በፊት የልጅነት መገለጫዎች በዋነኛነት ማልቀስ፣ መብላት፣ መጠጣት፣ መጸዳዳት እና መተኛት ናቸው። ወንድ ልጆች፣ ዕድሚያቸው ከ6 ወር እስከ 1 ዓመት ሲሆንስ? እንደ ጥናቶቹ ከሴቶች ይልቅ መላፋትን የሚወዱ እና በምልክት ጭምር ስሜታቸውን ለእናታቸው የሚገልጹ መሆን ይጀምራሉ። ወንዶቹ 2 ዓመት ሲሞላቸው ግን ከሴቶቹ ይልቅ ራሳቸውን በመግለጽ ቁጥብ ወደመሆን ያደላሉ። ዕድሜያቸው ከ4 እስከ 6 ሲደርስ ከሴቶች ባነሰ በፊታቸው ገጽ ስሜታቸውን የሚያሳዩ ይሆናሉ፤ ፊታቸውን ተመልክቶም ስሜታቸውን መገመትም አስቸጋሪ ይሆናል።[1]
በጊዜ ውስጥ በወንዶቹ ልጆች ላይ የምናየው ለውጥ ዋንኛ መነሾ ምንድን ነው? ጥናቶች የሚያሳዩት የወላጆች እና የአከባቢን ተጽእኖን ነው። ወላጆች ልጆቻቸው 1 ዓመት ከሞላቸው ጀምሮ ወንዶቹን እና ሴቶቹን የሚያስተናግዱበት መንገድ ይለያያል። ወንዶች ልጆቻቸው ስሜታቸው እንዲነቃቃ አይሹም፤ ስሜታቸው ችላ ማለትንም አባቶቻቸው በተግባር ምሳሌነትም ያሳዩዋቸዋል።
ስሜትን በፊት ገጽ የመግለጹ ነገር ከ4 እስከ 6 ዓመት ባለው ጊዜ ይበልጥ መቀነሱስ? የሚያያዘው ልጆች ከቤተ ሰቦቻቸው ውጭ ከሌሎች ልጆች እና ሰዎች ጋር መኅበራዊ ግንኙነት የጀመሩበት ከመሆኑ ጋር ነው። ልጆችም ቅድመ መደበኛ ትምህርት ይጀምራሉም። የትምህርት ቤት የመማሪያ መጽሀፍቶቹም ሴቶቹን አድራጊ ሳይሆን ተቀባይ፣ ራስ ገዝ ሳይሆን ተደጋፊ እና የሥራ መስኮቻቸውን የተወሰኑ አድርገው ይቀርጻሉ። ወንዶቹን ደግሞ የሚፈልጉትን ጠያቂ እና አስፈጻሚ አድርገዋቸው ይቀርባሉ። የቲሌቪዢን መስኮቶቹም የመጽሐፉቱን ገጸ ባህርያት ይደግሟቸዋል።[2] ቤት ውስጥ የተጀመረው ወንዶችን “ወንድ የማድረጉ ቀረጻ” ከቤት ውጭ በአስተማሪዎቹ በኩል እና በአቻዎቻቸው በኩል ተጠናክሮ ይቀጥላል። ወንዶቹ የሴቶቹን ያክል እንደ ፍርሀት እና ሀዘን ያሉ ስሜቶችን እንዳያሳዩ ይበረታታሉ፤ ካሳዩም ይቀጣሉ። ሴቶቹ በአንጻሩ እንዳሻቸው ስሜታቸውን እንዲገልጹ ይፈቀድላቸዋል። በሂደትም ኢመደበኛው የወላጆች እና የውጩ ዓለም ሥልጠና ወንዶች ስሜትን መግለጽን ወደመሸፋፈን እንዲያዘነብሉ ያደርጋቸዋል።
እየታደገ ሲመጣም ከዕድሜ አቻዎች ጋር የሚደረጉት ጫወታዎች ቤት እና ሰፈር የተጀመረውን የባህርይ ቀረጻ የበለጠ ያጸኑታል። የሴቶቹ ጫወታዎች ቅርርብ ላይ የተመሠረቱ እና ትሥሥር መገንባትን እና ማስቀጠልን ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ይሆናሉ። በእኛ ሀገር አውድ እቃቃን ማሰብ እንችላለን። በአንጻሩ የወንዶቹ ጫወታዎች ብዙ የቡድን አባል ያላቸው፣ ውድድርን ማሸነፍ ላይ ያተኮሩ፣ ጥንካሬን እና እንደ ቡድን አብሮ መሥራት ላይ ያተኮሩ ይሆናሉ። እንደ መሳሌ እግር ኳስን ወይም እርግጫን ማሰብ እንችላለን። እኚህን የወንድነት ባህርያትን የማያሳዩ ወንዶችስ ጭካኔ የተሞላበት ጉንተላን እና መገለልን ከዕድሜ አቻዎቻቸው ያስተናግዳሉ።
በሂደትም ማኅበረሰቡ ወንድነት የሚለውን ነገር ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ የበለጠ እየተቀበሉት ይመጣሉ። እዚህ ላይ የጾታዎቹ ሥነ ሕይወት ሲጨመርበት ወንድነት እና ሴትነት የተለያዩ የሕይወት ድርሻዎች ተደርገው ይታያሉ፤ የሌላውን ተግባር መፈጸምም የሚያሳፍር ይሆናል። ለወንድነት የተፈቀዱት ስሜቶች ልክ ያልተባሉት ይሆናሉ። የወንድ ልጅ ቁጣ የሚጠበቅ እና የሚፈለግ ተደርጎ ይታያል፤ ሴቷ በአንጻሩ ለስላሴ እንድትሆን ይጠበቅባታል። ከፍትወት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ፣ እንደ በአደባባይ መጎናተልን ያሉትን ጨምሮ፣ ለወንድ ይፈቀዳሉ። ማልቀስ እና ፍረሃት ያሉት ግን የወንድነት መታጣት ተደርገው ይሳላሉ። ስሜትን ማንጸባረቅ ሆነ ስሜታዊ ቅርርብን ማሳየትም “የእናቱ ልጅ” የሚል ያልተፈለገ ተቀጽላ ያስከትላል። አባትም ወደ ቤት ሲገባ ሴት ልጆቹ ሁሉ ከሳመ በኋላ ተራውን የሚጠብቀውን ወንድ ልጁን ግን እጁን በመዘርጋት ብቻ ያልፈዋል።
ውጤቱስ?
ተፈጥሮዋዊ ማንነቱ የሆነውን ነገር ወንድ ልጅን ከልክለነው ስናድግ እና ስሜትን መግለጽን ኃጢያት አድርገን ስናሳድገው ምን ይፈጠራል? የሚፈጠረው ነገር ለራሱም ሆነ አብረውት ላሉ ሰዎች መልካም አይሆንም። የራሱን ስሜት በቅጡ እንዳይረዳ አድርገን የኮተትነው ሰው ከሎች ሰዎች ጋር ባለው ቅርርብ እና ትሥሥር ውስጥ መግባባት ይቸግረዋል። በሌሎች ጫማ ሆኖ ስሜቶችን መረዳትም ዳገት ይሆንበታል። የሌሎችን ድካም ሲመለከትም ርህራሄ ከማሳየት ይልቅ ሲወቅስ እና ሲተችም ልናገኘው እንችላልን። እነዚህ ባህርያት ደግሞ መልካም ግንኙነት በሰዎች መካከል እንዲኖር እጅግ የሚያስፈልጉ ናቸው። እኚህን ማሳየት ያልቻለ ማንኛውም ሰው፣ ወንድም ይሁን ሴት፣ በቤተ ሰብ ውስጥ ሆነ ሌሎች ቅርርብን በሚፈልጉ የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ውስጥ ራሱ ተቸግሮ ሌሎችን እንደሚያስቸግር መገመት አይከብድም።
ስሜትን መረዳት እና መግለጽ ባለመቻሉ የሚጎዱት አብረውት ያሉት ሰዎች ብቻ ግን አይደሉም። ወንዱም ቢሆን ማህበረሰቡ ወንድ በሚል የሚጠብቃቸውን ገጸ ባህርያት ለመላበስ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ መጎዳቱ አይቀርም። እንደ አዕምሮ ጤና ላሉ ችግሮች ተጋላጭ የመሆኑ ዕድልም ከሴቶቹ ይልቅ ይሰፋል። ያፈነውን ስሜቱን ለመግለጽ የሚሄድባቸው አማራጭ መንገዶችም እንዲሁም አላስፈላጊ መዘዝ ይዘውለት ከተፍ ያላሉ። ለእጽ፣ ለቁማር እና ለወሲብ ፊልሞች ያለው ተጋላጭነትነትም ከሴቶች ይልቅ ይሰፋል። ነገሩ ሲከፋም ጸባይ ላይ ሁሉ እየተገለጠ ይመጣል፤ በቀላሉም የሚበግን እና ለጠብ የሚጋለጥ የመሆን ዕድሉም ይሰፋል። እገዛን መጠየቅም የድካም ምልክት ተደርጎ ስለሚወሰድም ከሌሎች በተፈላጊው ጊዜ ዕርዳታን ወንዶች የማግኘት ዕድላቸው ይጠባል። በጥቅሉ አደጋ ላይ የሚወድቀው ሁለ ነገራቸው ነው። ጤናቸው፣ ደስታቸው፣ ደህንነታቸው እንዲሁም ቤተ ሰቦቻቸው አደጋ ላይ ይወድቃሉ።
ምን ይሻላል?
የሚሻለው ማኅበረሰቡ ወንድነት የሚለውን ነገር ሁሉ ከመግዛት መቆጠብ ነው። ወንድ ስሜቱን ከመግለጽ በመቆጠቡስ እርሱም ሆነ ሌሎች እንደማያተርፉም መገንዘብም የለውጥ ሀሁ ነው። እንደ ወላጅ ወንድ ልጃችን ስሜቱን በገለጸ ቁጥር “ወንድ ሁን እንጂ” ፣ “ጠንከር በል፤ ወንድ ልጅ አያለቅስም” ዐይነት ንግግሮቻችን የሚያመጡትን ተጽዕኖ ልብ ማለት ያስፈልገናል። በወንድነት ስምም ወንድ ሙሉ ሰው እንዳይሆን እንዳናግደውም መጠንቀቅ ይገባናል። እውነታው ወንድነት ስሜትን መረዳትን እና መግለጽን አይከለክልም። ወንድነትም በቤት ውስጥ የትዳር አጋራችንን መንከባከብን እና ማገዝን አያስቀርም። እንደ ወንድ ስሜትን መረዳታችን እና መግለጻችን ደግሞም በምንችለው አቅም ለማገዝ መነሳታችንም ክብራችንን አይቀንስም።
በማኅበረሰባችን የሴት ባህርያት በሚል የተነፈግናቸውን እንደ ርህራሄ ያሉ ሰዋዊ ባህርያትን ለማጎልበትም የተዋጣለት መንገድ ህጻናት ልጆችን መንከባከብ ነው የለውጥ ጉዟችንን ከዛ እንጀምር፤ ለልጆቻችን እና ለትዳር አጋራችን በመገኘት የእውነት ወንድ እንሁን። ወተታቸውን ከማዘጋጀት ጀምሮ፣ ዳይፐራቸውን መቀየር፣ እሽሩር እያሉ ማስተኛትን ራሳችንን ማስለመድ በማኅበራዊ ግንኙነታችን ውስጥ ጭምር በብዙ ይለውጠናል። ጓዳ ውስጥም የምንችለውን ያክል ለማገዝ እንጣር፤ አጋሮቻችንም የተሻለ እንዲተኙ እንርዳቸው፤ በሚሠሩት ነገር በምንችለው ሁሉ በመሳተፍም ለሚሠሩት ነገር ዋጋ እና አክብሮትን እናሳይ።
[1] Ronald F. Levant “The Normative Male Alexithymia Hypothesis” in Ronald F; Levant, Shrana Pryo, Assessing and Treating Emotional Inexpressive Men (New York: Routledge, 2024), 1959-1963
[2] Parke, Ross D., Glenn I. Roisman, and Amanda J. Rose, Social development (New York: John Wiley & Sons, 2019), 415.
[3] Ronald F. Levant “The Normative Male Alexithymia Hypothesis” in Ronald F; Levant, Shrana Pryo, Assessing and Treating Emotional Inexpressive Men (New York: Routledge, 2024), 1959-1963
[4] Harper, Shaun R., and Frank Harris III, eds. College men and masculinities: Theory, research, and implications for practice (John Wiley & Sons, 2010), 306.
[5] Ronald F. Levant “Research on Normative Male Alexithymia and Related Phenomena” in Ronald F; Levant, Shrana Pryo, Assessing and Treating Emotional Inexpressive Men (New York: Routledge, 2024), 1965-1982
Written by : Dr. Tekalign Nega
Dr. Tekalign is the co-director of the Neighbor Love Movement that promotes love, justice, and flourishing across boundaries. He is a public intellectual passionate about human flourishing at the individual, institutional, and communal levels. His commentary on contemporary issues has been featured in numerous international and local media outlets, including The Economist, The Guardian, Fana TV, Walta TV, and Amhara TV.
Dr. Tekalign is a sought-after speaker and serves as an Assistant Professor at Addis Ababa University and a lecturer at the Ethiopian Graduate School of Theology. He is married to Tehitena Mesfin, has one son and one daughter. He is the author of My Neighbor(Rohobot, 2020) and The Prosperity Gospel: Turning a House of Prayer into a House of Merchandise (Rohobot, 2017). He has also written numerous articles addressing various issues.


Great Article
A very helpful read. Thank you for sharing.